የፍኖተ ሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ተችሏል።

4
ፍኖተ ሰላም: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ካሳነሽ አለኸኝ የፍኖተሰላም ከተማ ነዋሪ ናቸው። በፍኖተሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የወሊድ ክትትል ሲያደርጉ ነው አሚኮ ያገኛቸው።
በጤና ጣቢያው ከዚህ በፊት አልትራ ሳውንድ ባለመኖሩ እናቶች ወደ ግል ጤና ተቋማት በመሄድ አገልግሎቱን ያገኙ እንደነበር አንስተዋል።
በተለይም የጤና ጣቢያው ግቢ ለታካሚው ምቹ አልነበረም ብለዋል። አሁን ግን የጎደሉ ነገሮች ተሟልተው ጥሩ አገልግሎት እያገኙ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
ሌላኛዋ የፍኖተሰላም ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፈለጉሽ የትዋለ ከዚህ በፊት በጤና ጣቢያው በቂ መድኃኒት ባለመኖሩ ከውጭ በመግዛት ለአላስፈላጊ ወጭ ይዳረጉ እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን ችግሩ መቃለሉን ተናግረዋል። ቅዳሜ እና እሑድን ጨምሮ አገልገሎት እያገኙ መኾናቸውን አንስተዋል።
በፍኖተሰላም ጤና ጣቢያ በእናቶች ክፍል ውስጥ የሥነ ተዋልዶ ባለሙያ የትዋለ ፈጠነ በክፍሉ ውስጥ ከዚህ በፊት ያልነበሩ የማዋለጃ እና አልትራሳውንድ መሳሪያዎችን በማሟላት ወላድ እናቶች ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የፍኖተሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ኀላፊ ይሁኔ የኔዓለም ጤና ጣቢያው ከዚህ በፊት በርካታ ችግሮች ይስተዋሉበት እንደነበር ገልጸዋል።
የጤና ጣቢያውን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ተቋሙን ጽዱ፣ ማራኪ የማድረግ እና በግብዓት የማሟላት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
የሰው ኀይል እጥረት ችግር ግን አሁንም አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት ፈጥሯል ነው ያሉት።
የሰው ኀይል እጥረትን በመፍታ አገልግሎት አሰጣጡን በተሻለ ለመስጠት እየተሠራ መኾኑን የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አያልነህ ስንታየሁ ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ለሌላ ወጭ እና እንግልት እንዳይዳረግ ጥረቶች እየተደረጉ መኾናቸውንም አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሰላም የየትኛውም ማኅበረሰብ የጋራ ፍላጎት እንደኾነ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
Next articleየፍኖተ ሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ተችሏል።