
ደባርቅ: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር በወቅታዊ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የውይይት መድረክ በደባርቅ ከተማ አካሂዷል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ እንደገለጹት ማኅበረሰባዊ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በቅድሚያ የሰላም አማራጮችን መከተል ይገባል።
በትምህርት፣ በጤና፣ በምጣኔ ሃብት እና በሌሎችም ጉዳዮች እየደረሱ ያሉ ችግሮች ምንጫቸው የሰላም ችግር መኾኑንም አብራርተዋል።
የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እና ለታለመላቸው ሕጋዊ ዓላማ እንዲውሉ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በኩል ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ርብርብ ሊያደር ይገባል ብለዋል።
ማኅበረሰባዊ ተጠቃሚነትን እና ሀገራዊ ለውጥን ማረጋገጥ የሚቻለው በጦርነት አይደለም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የሰላም አማራጭን መከተል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ማኅበረሰባዊ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ምቹ የልማት ከባቢን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች ከየትኛውም ፖለቲካዊ አጀንዳ ነጻ በመኾን ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል።
በቀጣይም መንግሥት የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎችም በበኩላቸው ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የሰላም ችግሩ ያስከተለው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ከፍተኛ በመኾኑ ሊቆም ይገባል ነው ያሉት።
ሰላም የየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል የጋራ ፍላጎት በመኾኑ ቅድሚያ ለሰላም መስጠት እንደሚገባ አብራርተዋል።
በቀጣይም ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ግንባታ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!