
አዲስ አበባ: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት “ጉዞ ወደህዋ” በሚል መሪ መልዕክት ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ስር ባሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ እና ከፍተኛ ውጤት ያመጡ 150 ታዳጊዎችን በዋናው መሥሪያ ቤት በሚገኘው ማዕከል ውስጥ የተለያዩ የጽንሰ ሃሳብ እና የተግባር ሥልጠና በመስጠት አስመርቋል።
ተመራቂ ሠልጣኞች ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ከተውጣጡ በዘርፉ የላቀ ልምድ ባላቸው ተመራማሪዎች በሳተላይት ቴክኖሎጂ፣ አስትሮኖሚ፣ አስትሮፊዚክስ፣ በስፔስ እና ፕላኔታሪ ሳይንስ ላይ የጽንሰ ሃሳብ እና የተግባር ሥልጠና ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀምም ሀገራቸውን ለማስጠራት እንደሚሠሩ ነው ያስረዱት።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ቤተልሄም ንጉሤ በኢንስቲትዩቱ እየተሰጠ ያለው ሥልጠና እንደ ሀገር ለተያዘው የዲጂታላይዜሽን ጉዞ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለታዳጊ ሠልጣኞች ራሳቸውን እና ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት ሥልጠና ተሰጥቷል ነው ያሉት።
በተለይም የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ታዳጊዎች ካገኙት ሥልጠና በተጨማሪ ተቋሙ በሚያመቻችላቸው የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ሥልጠና እና ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ አዲስ አበባ ከሚገኘው ማዕከል በተጨማሪ ከክልል እና ከተማ መሥተዳደሮች የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በመተባበር በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ መሥተዳድሮች ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለሀገር ዕድገት እና ለውጥ እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል። ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤታማ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ሠለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!