“የመስቀል በዓል ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል”

4
ባሕር ዳር፡ መስከረም 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና የሕዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የመስቀል በዓልን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በክልሉ የሚከበሩ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የክልሉ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር ሢሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
የመስቀል በዓል ከሃይማኖቱ ተከታዮች ባለፈ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች የሚታደሙበት መኾኑን አንስተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ከፌዴራል እና ከክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በጥምረት በመኾን የመስቀል በዓል ያለምንም የጸጥታ ስጋት በሰላም እንዲከበር የተሟላ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በዓሉ በሰላም በሚከበርበት ጉዳዮች ላይ የጸጥታ ዕቅድ አዘጋጅቶ ግንዛቤም መሰጠቱን አንስተዋል። በዕቅዱ ላይ ውይይት ተካሂዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቁመዋል።
ስኬታማ ሰላም እና ደኅንነት እንዲኖር የጸጥታ ኃይሉ ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ በመስቀል በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው የእንግዳ አቀባበል ባሕሉ እንዲያስተናግድም ጠይቀዋል።
በበዓሉ አጠራጣሪ ሁኔታ ሲስተዋል ጥቆማ በመስጠት ትብብር ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ወንጀልን ለመከላከል የዳበረ አቅም አለው ያሉት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ለበዓሉ ፍጹም ሰላማዊነት የቴክኖሎጂ አቅሞችንም እንጠቀማለን ብለዋል፡፡
የፖሊስ ኃይሉ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር የተንቀሳቃሽ እና ቋሚ ጥበቃ ተመድቦ ተግባሩን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የመስቀል በዓል በሚካሄድባቸው ሥፍራዎች ሊከሰት የሚችልን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ የጸጥታ ኃይሎች ለሚያስተላልፉት መልዕክት የበዓሉ ታዳሚዎች እና አሽከርካሪዎች ቀና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኅብረተሰቡ ከፖሊስ የሚተላለፉ ክልከላዎችን በማክበር የሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አስገንዝበዋል።
የመስቀል ደመራ በሚደመርበት ወቅት የሕዝብን ሰላም የሚያውኩ ርችቶችን ወይም ማንኛውንም ተተኳሽ መተኮስ የተከለከለ መኾኑንም አሳስበዋል።
ጸረ ሰላም ኃይሎች በርችት ሰበብ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጥሩ ኅብረተሰቡ ለጸጥታ ኃይሉ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት በዓል እንዲኾንም ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የሲዳማ ሕዝብ የሕዳሴን መጠናቀቅ ውብ በሆነው የቄጣላ ሥርዓቱ ደምቆ በአደባባይ አክብሯል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤታማ መኾኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።