ትምህርትን በወቅቱ መከታተል እና ለፈተናዎች በቂ ዝግጅት ማድረግ ለጥሩ ውጤት ያበቃል።

2
ገንዳ ውኃ: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር የመተማ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት በ2017 ዓ.ም ካስፈተናቸው ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ካመጡት መካከል ተማሪ ኢስመተዲን ሙሐመድ እና ሳምራዊት አስምሮ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ውጤታማ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት በማምጣታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ ኮርሶችን በጊዜ ሰሌዳ ከፋፍለው በማጥናታቸው እና በቂ ዝግጅት በማድረጋቸው ጥሩ ውጤት እንዲመጣ አስችሏል ነው ያሉት።
በችግርም ውስጥ ኾነው ጠንክረው በመማር እና ጥሩ የትምህርት አቀባበል ስለነበራቸው የተሻለ ውጤት እዲያመጡ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን የተማሪዎች ጥረት ከፍተኛ ቢኾንም የወላጅ እና የመምህራን እገዛ ለውጤታቸው ከፍ ማለት አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው ያብራሩት።
ትምህርት ከተጀመረ አንስቶ ተማሪዎች በቀለምም ኾነ በሥነ ልቦና እንዲዘጋጁ ጥረት ማድረጋቸውን መምህራን አስረድተዋል።
በትርፍ ጊዜያቸው ወርክ ሽቶችን በማዘጋጀት፣ የማትሪክ ሽቶችን በመሥራት እና የአዳር ጥናት በማስጠናት ተማሪዎችን ለውጤት ማብቃታቸውን መምህራን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ለሚፈተኑ ተማሪዎችም የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ከወዲሁ ለማገዝ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማድረጋቸውን መምህራን ገልጸዋል።
ተማሪዎች በአዳር ጥናት ታግዘው የሚያስፈልጋቸው ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት እንዲያመጡ መሠራቱንም የምዕራብ ጎንደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደሳለኝ አያና ተናግረዋል፡፡
አቅም ያላቸውን ተማሪዎች በመምረጥ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሥራት ተማሪዎች እንዲማሩ ተደርጓልም ነው ያሉት።
ከባለፈው ዓመት በተሻለ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ከአሁኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ተማሪዎች በቂ ውጤት እንዳያመጡ ጸጥታው እንቅፋት እንደኾነባቸው ኀላፊው አንስተው በቀጣይም ይህን ችግር የመቅረፍ ኀላፊነት የሁሉም ማኅበረሰብ መኾኑን አቶ ደሳለኝ አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለ17 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
Next articleታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀደም ሲል የነበረውን የተሳሳተ ትርክት የቀየረ ነው፡፡