
ባሕር ዳር: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በባሕር ዳር ከተማ “በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርስን ጥቃት መከላከል እና ምላሽ መስጠት” በሚል መሪ መልዕክት ተሻሽሎ ከተቋቋመው ክልላዊ አሥተባባሪ አካል ጋር ውይይት አካሂዷል።
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል በተናጠል ከመሥራት ይልቅ በጋራ መሥራት ውጤት ላይ ያደርሳል በሚል ነው ውይይቱ የተካሄደው።
ችግሩን በመከላከል ዙሪያም የመግባቢያ ሰነድ ከአጋር አካላት ጋር የተፈራረሙ ሲኾን የተቋቋመው ክልላዊ አሥተባባሪ አካል በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን በተሻለ መንገድ ለመቀነስ የሚያስችል እንደኾነም ተገልጿል።
የፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመቀነስ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
ኀላፊው በባለፉት ጊዜያት ላይ ተከስተው የነበሩትን የሴቶች እና ሕጻናት ጥቃት በተያዘው ዓመት መቀነስ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአምስት ሴቶች ውስጥ አንዷ ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባት በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል ያሉት ዶክተር አያሌው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ችግሩ የከፋ መኾኑን አመላክተዋል።
በጉዳዩ ላይ ሁሉም አካል ርብርብ ማድረግ እንደሚገባውም ነው ያስረዱት፡፡ ወንጀሉን ፈጽመው በተገኙ አካላትም ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!