
ከተጠየቀው የአፈር ማዳበሪያ እስከዚህ ወቅት 59 በመቶ ብቻ መግባቱንም የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
አቶ ቢራራው ተሾመ እና ቁምላቸው አወቀ የበየደ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ ለምርት ዘመኑ ደጋግሞ በማረስ ማሳቸውን ዝግጁ ቢያደርጉም የስንዴ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት በመከሰቱ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ የመኽር ወቅቱ እንዳያልፍባቸውም ወደተለመደው ልማዳዊ አሠራር ለመግባት እየተገደዱ መሆናቸውን ነው አርሶ አደሮቹ የተናገሩት፡፡ በአካባቢው ዘር ለመጠቀም መወሰናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የምርጥ ዘር ዋጋም አምርተው ከሚያገኙት ጋር ያልተመጣጠነ ከፍተኛ በመሆኑ ደፍረው እንዳይገዙት እያደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
የበየዳ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሸጋው ብርሃን ‘‘የግብዓት በተመጣጣኝ ዋጋ አለመቅረብና የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በወቅቱ አለመቅረብ የግብርናውን ምርታማነት ይፈትነዋል’’ ብለዋል፡፡ ወደ ገጠር ቀበሌዎች የሚያደርሱት መንገዶችም በጎርፍ ምክንያት ጉዳት ስለደረሰባቸው በወቁቱ ለማሰራጨት መቸገራቸውን ተናግረዋል።
ዩሪያና ዳፕ በተቆራረጠ መንገድ በመምጣቱ ወደገጠር ቀበሌዎች ለማመላለስ የሚደረገውን ጥረት አዳጋች እንዳደረገባቸው ያስታወቁት ኃላፊው ግብዓት በማኅበራት በኩል እንዲቀርብ መደረጉንም ነው አቶ ሸጋው የገለጹት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አራጋው ገብረማሪያም በዞኑ በ2012/13 የምርት ዘመን ለማቅረብ ከታቀደው የአፈር ማዳበሪያ እስከ ግንቦት1/2012 ዓ.ም 59 በመቶ ብቻ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ ከ37 ሺህ 200 ኩንታል በላይ ደግሞ ለአርሶ አደሩ መሠራጨቱን የተናገሩት ኃላፊው በዞኑ የጠለምት ወረዳ ‘ኤን ፒ ኤስ ዚንክ ቦሮን’ የተባለው የአፈር ማዳበሪያ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው እስከ ግንቦት 1/2012 ዓ.ም አለመግባቱ የግብርና ሥራውን ፈተኝ እንዳደረገባቸው ገልጸዋል።
በዞኑ በ2012/13 የምርት ዘመን ከታቀደው 3 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር 2 ሺህ ኩንታሉ ተመድቧል፤ 635 ኩንታሉም ለአርሶ አደሩ መሠራጨቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ አራጋው 80 በመቶ የሚሆነው የዞኑ የዘር ወቅት ከዚህ በኋላ በመሆኑ ቀሪውን ዘር በፍጥነት ለማሰራጨት ከክልሉ ጋር መነጋገራቸውን ነው ያስታወቁት። ከሰንዴና ሌሎች የግብዓት እጥረቶች በተጨማሪ የበቆሎ እና የቢራ ገብስ የዘር እጥረት ማጋጠሙንም አመልክተዋል፡፡ የቢራ ገብስ ደግሞ በተሻሉ የአካባቢ ዘርያዎች መሸፈን መቻሉን አቶ አራጋው ተናግረዋል፡፡ ችግሩም በአማራ ምርጥ ዘር ኢንተር ፕራይዝ ጭምር መከሰቱን ነው የገለጹት።
በግብዓት ላይ የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ ከአርሶ አደሮች አቅም በላይ ሆኗል ለተባለው ጥያቄም ለትራንስፖርት ከተደረገ ጭማሪ ባለፈ የተጋነነ ጭማሪ አለመኖሩን ኃላፊው ገልጸዋል።
በዞኑ በ2012/13 ዓ.ም የመኽር ወቅት 123 ሺህ ሄክታር መሬት ይታረሳል ተብሎ ይጠበቃል። ከ73 ሺህ 800 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ሲሰራጭ ፤ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል። የግብዓት እጥረቱ የታለመውን ዕቅድ ለማሳካት ፈተና እንዳይሆን ግን ሥጋት ተፈጥሯል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ
ፎቶ፡- ከድረገጽ