
ባሕር ዳር: መስከረም 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እምቅ አቅም ካላቸው ሀገራት ውስጥ ትጠቀሳለች። ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የግብርና ምርት ነው።
ከምታመርታቸው የግብርና ምርቶች ውስጥ በርበሬ አንዱ ነው። በኢትዮጵያ በዚህ ምርት የሚታወቁ በርካታ አካባቢዎችም ይገኛሉ። በርበሬ ምርት ከሚታወቁ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል አንደኛው ነው። ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በየዓመቱ ከ76 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበርበሬ ይሸፈናል። በሄክታር ከ18 እስከ 20 ኩንታል ምርት ይገኛል።

በአማራ ክልል የበርበሬ አምራች ከኾኑት ዞኖች መካከል የምዕራብ ጎጃም ዞን አንዱ ነው። በዞኑም ወንበርማ፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፣ ጃቢ ጠህናን እና ደንበጫ ወረዳዎች በስፋት በርበሬ በማምረት ተጠቃሽ ናቸው።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር የበርበሬ ምርት ለገበያ አዋጭ ሰብል እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ በ2017 የምርት ዘመን በሄክታር ከ15 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ነግረውናል፡፡ በአሁኑ የገበያ ዋጋ በገንዘብ ሲሰላም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ይኾናል ነው ያሉት፡፡ የበርበሬ ምርት ትኩረት ተሰጥቶ ከተሠራበትም በሄክታር እስከ 20 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ በሦሥት ሄክታር መሬት ላይ በርበሬ እያለሙ መኾኑን ተናግረዋል። ከዚህም እስከ 60 ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅደዋል፡፡ ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲነጻጸር በርበሬ ገቢው የተሻለ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ በአካባቢው በርበሬ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ኑሯቸውን እየቀየሩ መኾኑንም ነግረውናል፡፡
የበርበሬን ምርታማነት የሚጎዳው በሰብሉ ላይ የሚከሰት በሽታ መኾኑን አንስተዋል። እስከ አሁን የተሻለ መድኃኒት አለመገኘቱንም ተናግረዋል፡፡ ሰብሉን በሽታ ካጠቃው አክሳሪ በመኾኑ ይህንን በመፍራት የአምራች አርሶአደሮች ቁጥር መቀነሱን ገልጸዋል፡፡ የተሻሻለ የበርበሬ ዝርያ እንዲቀርብም ጠይቀዋል።
ሌላው የበርበሬ አምራች አርሶ አደር የበርበሬ ምርት አዋጭ እና ለገበያ ተፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል። በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ በርበሬ እያለሙ እንደኾነም ነግረውናል፡፡ በበርበሬ ሰብል ላይ የሚከሰተውን በሽታ ለመከላከል ጥረት እንደሚያደርጉም አንስተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አግማስ አንተነህ እንደገለጹት በዞኑ 21 ሺህ 980 ሄክታር መሬት በበርበሬ ምርት ይሸፈናል። ከዚህ ውስጥ 17 ሺህ 940 ሄክታሩ በኩታ ገጠም የሚለማ ነው ብለዋል።
በርበሬ አዋጭ እና ገበያ ላይ ተፈላጊ በመኾኑ በኪሎ ግራም እስከ 700 ብር እየተሸጠ መኾኑን ተናግረዋል። ይህ ከፍተኛ ዋጋ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ በማድረግ ኑሯቸውን እንዲለውጡ እና ሃብት እንዲያፈሩ እየረዳቸው መኾኑንም አክለዋል።

ምንም እንኳን በርበሬ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ቢኾንም በምርቱ ላይ የሚከሰት በሽታ ዋናው ስጋት ኾኖ ቀጥሏል።
በሽታው ሰብሉን ካጠቃው ኪሳራ የሚያስከትል በመኾኑ አንዳንድ አርሶ አደሮች ከበርበሬ ምርት ይወጣሉ። ለበሽታው የተሻለ መድኃኒት አለመኖሩም ሌላው ችግር ነው።
ይህን ችግር ለመፍታት የግብርና ባለሙያዎች በሽታው ከመከሰቱ በፊት ሰብል ማፈራረቅ፣ የተመረጡ ዘሮችን መጠቀም እና የተለያዩ የመከላከያ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው እንዳሉት ለበርበሬ አምራች አርሶ አደሮች በተባይ ቁጥጥር እና አሰሳ ዙሪያ ሥልጠና ከመስጠት በተጨማሪ የገበያ ትስስርም እየተፈጠረላቸው ነው።

በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው እየለማ ያለው “ማረቆፋና” የተባለ የበርበሬ ዝርያ ነው። ይህ ዝርያ አካባቢውን በመላመድ ምርታማነቱ ከፍተኛ እና ለገበያም ተፈላጊ መኾኑ ተገልጿል።
በአማራ ክልል በዚህ ዓመት ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበርበሬ ተሸፍኗል። በቀጣዩ የምርት ወቅት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የበርበሬ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ደግሞ በክልሉ የሚታየውን የበርበሬ ዋጋ ንረት ለመቀነስ እና ምርቱ ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ ኢኮኖሚውን በመደገፍ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ተጠቅሷል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!