
ባሕር ዳር: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰዎች ከሕግ ሲያፈነግጡ እና ከኔ በላይ ጉልበታም ላሳር ነው ሲሉ ዛቻን እንደ መሳሪያ ይጠቀማሉ። መልካም የኾነ መፍትሔን እና የመነጋገር ባሕልን ወደጎን በመተው በጉልበት እና በማንገራገር የሚፈልጉትን ለማስፈጸም የሚሞክሩ ሰዎች የሚከውኑት ተግባርም ነው ዛቻ።
ይሁንና ዛቻ በሕግ የማይደገፍ ይልቁንም እንደተፈጸመው የዛቻ አይነት እና መጠን ሊያስጠይቅ እና እስከ መቀጣት ሊያደርስ የሚችል ተግባርም ነው።

አቶ መሥፍን መኮነን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሕግ ምክር፣ ሕግ ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት የክልል አቃቢ ሕግ ናቸው። ዛቻ ማለት ማንም ሰው በሌላ ሰው ላይ ፍርሃትን ወይም ድንጋጤን በሚቀሰቅስ ሁኔታ ከባድ አደጋ ወይም ጉዳት የሚያደርስበት መኾኑን መግለጽ ማለት ነው ብለዋል።
ዛቻን የሚመለከቱ ሁለት ሕጎች አሉ ይላሉ አቃቢ ሕጉ። አንደኛው የኮምፒውተር ወንጀልን መከላከል በሚል የተደነገገው አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ አንድ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 580 ላይ የተቀመጠው ተራ ዛቻ ወይም የቃል ዛቻ ነው ይላሉ። ዛቻን በተመለከተ በሁለቱ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ተተንትኖ ይገኛል ነው ያሉት። አንቀጽ 580 እንደሚያትተው ጉዳዩ የሚቀርበው በግል ተበዳይ አቤቱታ እንደኾነ ተቀምጧል ብለዋል። ሁለት አይነት የአቤቱታ አቀራረብ አለ። አንደኛው በግል ተበዳይ መሠረት የሚቀርብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በወንጀል ክስ መሠረት የሚቀርብ አቤቱታ ነው ብለዋል።
ለተበዳይ አቤቱታ የሚቀርብ ክስ ተበደልኩ የሚል ሰው ወደ መርማሪ ፖሊስ ሄዶ የሚያቀርበው እንደኾነ ነው የተናገሩት። የወንጀል ክስ ግን የተበደለው ሰው ወደ መርማሪ ፖሊስ መሄድ ሳይጠበቅበት በመርማሪ ፖሊስ እና በአቃቢ ሕግ አማካኝነት የሚታይ ወንጀል እንደኾነ ነው የገለጹት። ከዚህ አንጻር ተራ ዛቻ ወይም የቃል ዛቻ አንቀጽ 580 ላይ በተቀመጠው መሠረት በግል አቤቱታ የሚቀርብ ነው ብለዋል አቃቢ ሕጉ።
በተራ ዛቻ እና በኮምፒውተር ዛቻ መካከል አንድነትም ልዩነትም አለ፤ አንድነታቸው በሁለቱም ዛቻ እና ማስፈራሪያ መኖሩ እንደኾነ ነው የገለጹት። ልዩነታቸው ደግሞ 580 የሚጠቅሰው የዛቻ አይነት በቃል የሚደረግ ማስፈራሪያ ነው። ይህም ከ500 ብር የማይበልጥ የገንዘብ ቅጣት እና ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ሊያስቀጣ እንደሚችል ነው የተናገሩት። የኮምፒውተር ዛቻን በተመለከተ ደግሞ የተደነገገው አዋጅ ቁጥር 958/2008 ላይ የተቀመጠ ነው ብለዋል። ማንኛውም ሰው ኾን ብሎ የኮምፒውተር ሥርዓትን በመጠቀም በጽሑፍ፣ በንግግር፣ በቪድዮ እና በስዕል አማካኝነት የሚፈጸም እንደኾነ ይተነትናል ነው ያሉት። ይህም ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና እንደ ወንጀሉ ክብደት እና ቅለት ታይቶ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ድረስ እንደሚያስቀጣም አብራርተዋል።
የኮምፒውተር መሣሪያዎች በመታገዝ የሚደረግ ዛቻ የቅጣት መጠኑ እንደሚበልጥም አስገንዝበዋል። ለምን ቢባል የዛቻው ተደራሽነት እና የሥርጭት መጠኑ ከፍተኛ ስለሚኾን ነው ብለዋል። ተራ ዛቻ የግል ተበዳይን መሠረት አድርጎ የሚፈጸም በመኾኑ ከታረቀ እና ከተስማማ ሕጉ ይፈቅዳል ነው ያሉት። የሳይበር ወይም የኮምፒውተር ዛቻ ከኾነ ግን የወንጀል ክስ በመኾኑ እና ዛቻው በሌላ ማኅበረሰብ ላይም የሚያሳድረው ተጽዕኖ ሊኖር ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ በእርቅ ላይዘጋ ይችላል ነው ያሉት። ምናልባትም በዳይ እና ተበዳይ ቢታረቁ እንኳ የቅጣት መጠኑን ሊቀንሰው ይችላል እንጅ ክሱን ሊያስቀር አይችልም ነው ያሉት።
ተበደልኩ የሚል ሰው ክስ ሲያቀርብ ማስረጃ ሊኖረው ይገባል የሚሉት አቃቢ ሕጉ በሳይበር ዛቻ ጊዜ የዛቻው ቅጅዎች፣ የዛቻው ቀን፣ የዛቻው ሰዓት እና በምን አይነት አማራጭ ዛቻው እንደተካሄደበት ማቅረብ ይኖርበታል ነው ያሉት። አሁን ላይ ከግለሰብ አልፎ ብሔርን፣ ዘርን፣ ቀለምን እና ሌሎች መለያዎችን መሠረት ተደርጎም ዛቻ ይስተዋላል የሚሉት አቃቢ ሕጉ እነዚህን ሁሉ ሕጉ ተጠያቂ እንደሚያደርግ አንስተዋል።
ብሔርን ፣ ዘርን እና ቀለምን መሠረት አድርገው የሚነሱ ዛቻዎች በሌሎች ተጨማሪ ሕጎችም ሊታዩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ዛቻ እንዲህ አደርግሀለሁ ብሎ ስለኾነ የሚዝተው ከፍ ወዳለ ወንጀልም የማደግ ነገር ስላለው በሕጉ በትኩረት ሊታይ የሚችል እንደኾነ ነው የገለጹት።
ሰው የሚናገረው ያሰበውን ነገር ነውና ሃሳቡ ወደ ተግባር ተቀይሮ ለከባድ ወንጀል ሊዳርግ ይችላል ብለዋል። ሰዎች ዛቻን ቀለል አድርገው ማየት እንደሌለባቸውም አንስተዋል። ምክንያቱም ጥንስስ ሃሳብ ነው አድጎ ወንጀል ሊኾን የሚችለው ብለዋል። ዛቻ የተፈጸመበት ሰው ብቻ ሳይኾን ዛቻ ፈጻሚውም ቀድሞ ሊጎዳ ይችላል፤ ስለኾነም ዛቻ በግለሰብ ላይ እና በማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ መዘዝ ሊያመጣ እንደሚችልም መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሰዎች ዛቻ ሲፈጸምባቸው ለሚመለከተው የፖሊስ አካል ማሳወቅ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። መታወቅ ያለበት ግን ዛቻ ፈጻሚውም ቢኾን ተጎጅ የሚኾንበት መንገድ ስላለ ከድርጊቱ መቆጠብ ነው መፍትሔው ብለዋል።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!