የባሕር በር ያስፈልገናል ስንል ለቅንጦት አይደለም።

10
ባሕር ዳር: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ የባሕር በር አልባ ሀገራት መካከል በሕዝብ ቁጥር ብዛት ከፊት የምትቀመጥ ሀገር ናት።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ባለፉት 30 ዓመታት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ኖሯቸው የባሕር በር አልባ የኾኑ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር የሚስተካከሉ አይደሉም። ሀገሪቷ ባልተገባ መንገድ የባሕር በር አልባ ኾና ጥቅሟን ስታጣ ቆይታለች። አሁን ላይ ይህ ፍትሃዊነት የጎደለው አካሄድ መቆም ይገባዋል በሚል ድምጿን እያሰማች ነው። አሚኮ ይህንን በተመለከተ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያን ጠይቋል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪው ትዕዛዙ አያሌው “የባሕር በር ያስፈልገናል ስንል ለቅንጦት አይደለም” ይላሉ። ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የማይገባትን ዋጋ ስትከፍል ቆይታለች ነው ያሉት። ይህ ግን አሁን ሊበቃ ይገባዋል ይላሉ። ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ በመኾኗ በሦስት ዓበይት ጉዳዮች ጉዳትን ስታስተናግድ መቆየቷንም አንስተዋል። እነኝህ ሦስት ጉዳዮችም የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ እና የሀገሪቷ የዲፕሎማሲ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ከብሔራዊ ደህንነት አኳያ ኢትዮጵያ የትኛውንም ፍላጎቷን ለማሟላት ጥረት ስታደርግ የራሷን የውስጥ ጉዳዮች ለሦስተኛ ወገን አጋላጭ አድርጋ ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ የትኛውም ዓይነት የመንግሥት እና የሕዝብ ፍላጎቶችን ለማሟላት ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶች ወዳጅም ጠላትም ለኾኑ ሀገራት ተጋላጭ ናቸው ነው ያሉት። ይህም የሀገሪቱን የሉዓላዊነት እንዲሁም የደህንነት ጉዳይ አደጋ ውስጥ የሚጥል ስለመኾኑም አስረድተዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ በሁለት መንገድ ኢትዮጵያ ጥቅሟን አጥታለች የሚሉት አቶ ትዕዛዙ አያሌው በአንድ በኩል ለወደብ የሚከፈል ከፍተኛ የኾነ ገንዘብ እና በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚመጡ አልሚዎችን ፍላጎት የገታ ነው ብለዋል። ይህም ጥቅል ውጤቱ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ክፉኛ ተጎጅ እንዲኾን አድርጎታል ነው ያሉት። የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር በር ባለቤት ከኾኑት ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በባሕር በር በአማካኝ እስከ 1 ነጥብ 5 በመቶ ዓመታዊ እድገት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው መረዳት ይቻላል ነው የሚሉት።
የባሕር በር አልባ መኾናችን በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሚና ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም ብለዋል የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ። ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ ሀገራት በሰጥቶ መቀበል መርሕ የሚደራደሩ በመኾናቸው ኢትዮጵያ ለዚያ ብቁ ኾና ሊያገኟት አልቻሉም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ የባሕር በር ባለመኖሩ ስለመኾኑ ነው ያስረዱት። እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ሲታዩ “የባሕር በር ያስፈልገናል ስንል ለቅንጦት አለመኾኑን ያረጋግጡልናል ብለዋል። ኢትዮጵያ ባልተገባ መንገድ ታሪካዊ ሃብቷን አጥታለች የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ትዕዛዙ አያሌው በኔ እምነት የብዙ ሀገራት የትኩረት ማዕከል በኾነው ቀጣና ተቀምጠን ያለ ባሕር በር ረዥም ርቀት መጓዝ አንችልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ፍላጎት ወደብን በኪራይ መያዝ እና ማልማት አይደለም የሚሉት መምህሩ ኢትዮጵያ በባለቤትነት የምታሥተዳድረው የባሕር በር ያስፈልጋታል ብለዋል። የዓለም አቀፍ አካሄዶችን በመፈተሽ መንግሥት በተጠና መንገድ መጓዝ አለበትም ነው ያሉት። በሂደቱ ውስብስብ ጉዳዮች ሊያጋጥሙ ይችላሉም ብለዋል። እነዚህን ችግሮች በላቀ የፖለቲካ አመራር እና የዲፕሎማሲ ብልጫ ዳር ለማድረስ ሊሠራ እንደሚገባ ነው ያነሱት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግም ኢትዮጵያ የተነጠቀችው የባሕር በር ወይንም ወደብ ብቻ ሳይኾን በባሕር ውስጥ ያሉ ትልልቅ ሃብቶችን ጭምር ነው ብለዋል።
የባሕር በር ያስፈልገናል በሚለው ጉዳይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚግባባበት እንደሚኾን እገምታለሁ የሚሉት መምህሩ ለዚህ ታላቅ ተግባር እውን መኾን የዜጋ ዲፕሎማሲን ጨምሮ የመንግሥት መደበኛ የዲፕሎማሲ አካሄድ በተጠና መንገድ ሊከናወን ይገባዋል ብለዋል።
ለዚህ ተግባር እንቅፋት ሊኾኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በማጥናትም አስቀድሞ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ኤልያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሕዳሴ በጋራ ችለናል የሚለውን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን እና አቋማችንን በጉልህ ያሳየ ነው።
Next articleየዛቻ የሕግ ተጠያቂነት እስከምን ድረስ ነው?