ለሰላም ዘብ በመቆማቸው የልማት ተሳታፊም ተጠቃሚም መኾን እንደቻሉ የኮምቦልቻ ከተማ ሴቶች ገለጹ።

6

ደሴ: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኮምቦልቻ ከተማ ከሚገኙ የተለያዩ የሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በሰላም፣ በልማት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡

 

ለአሚኮ አስተያየታቸውን የሰጡት የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሕይወት ካሳ በሴቶች ልማት ኅብረት ተደራጅተው በሰላም፣ በቁጠባ እና ሌሎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር እርስ በእርስ በመረዳዳት ኑሯቸውን እያሻሻሉ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

 

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ራህማ ሙሀመድ “ልጆቻችንን፣ ቤተሰቦቻችንን እና ጎረቤቶቻችንን ስለሰላም በመምከራችን የልማት ተሳታፊ እና ተቋዳሽ መኾን ችለናል” ብለዋል፡፡

 

የኮምቦልቻ ከተማ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ አመዘን ሙሀመድ ሴቶችን በከተማ ግብርና፣ በዶሮ እርባታ እና በሌሎች የገቢ ማስገኛ አማራጮች በማሰማራት ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

 

ሴቶችን በስፋት ተጠቃሚ ለማድረግ እያጋጠመ ያለውን የብድር እና የመሥሪያ ቦታ ችግር ለመፍታት በበጀት ዓመቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

 

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድአሚን የሱፍ የኮምቦልቻ ከተማ እና አካባቢው ሰላም እና ልማት እንዲፋጠን የከተማው ሴቶች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

 

በከተማው የተጀመሩ ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ በ2018 በጀት ዓመት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡

 

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ በክልሉ ያለው የሰላም እጦት በሰዎች ላይ በተለይም በሴቶች፣ ሕጻናት እና አረጋዊያን ላይ በርካታ ማኅበራዊ፣ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማድረሱን አንስተዋል፡፡

 

አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ሴቶችን በልማት ኅብረት በማደራጀት ከኢኮኖሚ ተኮር መሥሪያ ቤቶች እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ስለመኾኑም ቢሮ ኀላፊዋ ተናግረዋል ፡፡

 

ተቋማት አዲስ በተዘጋጀው አሻጋሪ ዕቅድ የሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ ወጣቶችን እና ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ተጠቃሚ ስለማድረጋቸውም ልዩ ክትትል ይደረጋል ብለዋል ቢሮ ኀላፊዋ።

 

ክልሉ ወደ ተሟላ ሰላም እንዲሸጋገር የሴቶች በተለይም የእናቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት ወይዘሮ ብርቱካን አሁንም ሰላም እንዲረጋገጥ ከቤት ጀምረው ጫካ የገቡ ወገኖችን በመምከር እና በመመለስ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየምዕራብ ጎጃም ዞን ገቢዎች መምሪያ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ አቅዶ እየሠራ ነው።
Next article“የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር በመስቀሉ የተደረገልንን በማሰብ ሊኾን ይገባል” ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ