
ፍኖተ ሰላም፡ መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ገቢዎች መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል።
መምሪያው በ2017 በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች 2 ቢሊዮን 332 ሚሊዮን ብር ለመሠብሠብ አቅዶ 1 ቢሊዮን 5 መቶ ሚሊዮን ብር ገቢ መሠብሠቡን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ግዛቸው ካሴ ተናግረዋል።
የገቢ አሠባሠቡን በተሻለ ለማከናወን በዞኑ ሁለት ከተማ አሥተዳደሮች እና ሁለት ወረዳዎች ላይ የዲጂታል ገቢ አሠባሠብ ዘዴ ተግባራዊ እየተደረገ መኾንም አንስተዋል።
መምሪያ ኀላፊው እንዳሉት በ2018 በጀት ዓመት በዞኑ በአጠቃላይ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ ብር ለመሠብሠብ እየተሠራ መኾኑን እና እስካኹንም ከ306 ሚሊዮን በላይ ገቢ መሠብሠቡን ገልጸዋል።
አቅምን አሟጦ በመጠቀም እና የተሻለ ገቢ በመሠብሠብ የ25 ዓመት አሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት እቅድን እውን ለማድረግ ይሠራልም ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጃቢ ጠህናን ወረዳ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መልካሙ ስንታየሁ እንዳሉት ባለፈው በጀት ዓመት በወረዳው ከ183 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሠብ በማቀድ 168 ሚሊዮን ብር መሠብሠቡን ተናግረዋል።
የፀጥታ ችግሩ በገቢ አሠባሠቡ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ቢፈጥርም በመሪዎች እና በባለሙያዎች በተደረገ ቅንጅት ገቢውን ለመሠብሠብ ተችሏል ብለዋል። በችግርም ውስጥም ቢኾኖ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
የሽንዲ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተመስገን አማን አካባቢው ለተራዘመ ጊዜ በፀጥታ ችግር ውስጥ ቢቆይም ከተለያዩ የገቢ አማራጮች በመሠብሠብ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ በ2018 በጀት ዓመት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሠብ አቅዶ እየሠራ ነው ብለዋል። እስካሁንም ከደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሠብሠብ አቅዶ ሙሉ ለሙሉ መሠብሠብ መቻሉን ኀላፊው ተናግረዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት በተሠበሠበው ገቢ የልማት ሥራዎችን መሥራት መቻሉ የዚህን ዓመት የገቢ አሠባሠብ ውጤታማ አድርጎታል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!