
ወልድያ: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ ግብርናን በማዘመን ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
መምሪያው የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅን በወልድያ ከተማ አካሂዷል።
የመምሪያው ኀላፊ ተገኘ አባተ የዞኑን የግብርና ዘርፎች በማዘመን በምግብ ራስን የመቻል ፍጥነትን ለማሳለጥ ታቅዷል ብለዋል። ለዚህም አርሶ አደሮች ከዝናብ ጠባቂነት ወጥተው በመስኖ እንዲያመርቱ ያሉትን የመስኖ አማራጮች ሁሉ ተጠቅሞ ማምረት የሚቻለበት ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል።
በመኾኑም በ2017 በጀት ዓመት በመስኖ ይለማ ከነበረው 20 ሺህ ሄክታር መሬት በ2018 ወደ 23 ሺህ ሄክታር መሬት ከፍ እንዲል ታቅዷል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የአስተራረስ ሥርዓቱ ከበሬ ተላቅቆ በትራክተር ማረስ የሚቻልበት አቅምን ለማጎልበት በ2018 በጀት ዓመት ትራክተሮች ለአርሶ አደሮች ይሠራጫሉ ብለዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና ልማትን ከኢኮኖሚ ምንጭነት ጋር በማጣመርም ይሠራል ነው ያሉት።
ቆላማውን የዞኑን ቀጣና የአትክልት እና ፍራፍሬ ቀጣና የማድረግ ዕቅዱ በስኬት እንዲፈጸም በስፋት የችግኝ ሥርጭት ይካሄዳል ያሉት ኀላፊው ደጋማውን አካባቢ በአፕል እና በሌሎች የደጋ ፍራፍሬዎች እንዲሸፈን ይሠራል ብለዋል።
ከሰብል ምርት አኳያ በ2018 በጀት ዓመት ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዷልም ነው ያሉት። ይህም ካለፈው በጀት ዓመት አንጻር ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ልዩነት አለው ብለዋል። ይህን ምርት ለመሠብሠብ የግብዓት አቅርቦት፣ የሰብል ክትትል እና ዘመናዊ ግብርና ተግባራዊ ይደረጋሉ ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!