
ባሕር ዳር: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ መሟላት ስለሚገባቸው የጽዳት እና ንጽሕና ጉዳዮች ዙሪያ ከሃይማኖት ተቋማት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል ተቋማት የየራሳቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በአማራ ክልል የኮሌራ ወረርሽኝን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም መቀነስ እንደተቻለ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ከቁጥጥር ውጭ እንዳልኾነም አንስተዋል። በሽታውን “በክልሉ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት እየተሠራ መኾኑንም” አንስተዋል።
ወረርሽኙ የሚበዛው ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች መኾኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ በሽታው እንዳይስፋፋ የሃይማኖት ተቋማት ማሟላት ስለሚጠበቅባቸው የውኃ፣ የጽዳት እና የንጽሕና መስፈርቶችን መሠረት ያደረገ ሰነድ መዘጋጀቱንም አመላክተዋል።
የኮሌራ በሽታን ለማጥፋት የሃይማኖት ተቋማት ከጤና ተቋማት ጋር መሥራት እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል። በተለይም የሃይማኖት ተቋማት በባለቤትነት ይዘው ወረርሽኙን ለመከላከል ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ኮሌራን በዘላቂነት ለማጥፋት ቋሚ አሠራርን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል። የሃይማኖት ተቋማት እንደ ሌሎች ተቋማት የራሳቸው መሥፈርት ኖሯቸው እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
የምክክር መድረኩ ለሁለት ቀናት እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!