ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት መፍጠር በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠበቅ ተግባር ነው። 

4

ደብረ ብርሃን: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ፍትሕ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ነው።

 

በ2017 በጀት ዓመት በሰሜን ሸዋ ዞን የተሻለ የፍትሕ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ በተሠራው ተግባር አበረታች ውጤት መመዝገቡን የመምሪያው ኀላፊ ደመረ ቸሬ ገልጸዋል።

 

ይሁን እንጂ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ውስንነቶችን ማስተካከል፣ የፍትሕ ማዘግየት እና የተደራሽነትን ችግር መቅረፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዞኑ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር በትጋት መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።

 

ፈጣን፣ ውጤታማ፣ ተደራሽ እና በሕዝብ ዘንድ ታማኝነት ያለው የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት የተለያዩ ተግባራት መከናወኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ናቸው።

 

የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞችን አቅም የማሳደግ፣ በወንጀል የተመዘበረን የመንግሥት ሃብት ማስመለስ፣ ለወንጀል ጠቋሚዎች እና ምስክሮች የሕግ ከለላ የመስጠት፤ ከሌሎች የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት የመሥራት እና ተከራክሮ የማሸነፍ ውጤታማነትን ማሳደግ ተጠቃሽ ተግባራት እንደነበሩም አብራርተዋል።

 

ማኅበራዊ ፍትሕን የማረጋገጥ፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማክበር እና ማስከበርም ይጠቀሳሉ ነው ያሉት።

 

ይሁን እንጂ ያደገ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ጠንካራ እና ታማኝነት ያለው የፍትሕ ሥርዓት የመገንባት፣ ሕግ አክባሪ እና ወንጀል ጠል ማኅበረሰብ የመፍጠር እና ለፍትሕ ፈላጊ ማኅበረሰብ እርካታ መፍጠር የሚያስችል ብቃት እና ዕውቀት ያለው መሪ እንዲሁም ባለሙያ መፍጠር ላይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መኾኑንም አስገንዝበዋል።

 

በ2017 በጀት ዓመት የነበሩ ጥንካሬዎችን ይበልጥ በማሳደግ እና ክፍተቶችን ፈጥኖ በማስተካከል በክልሉ “ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት መፍጠር በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠበቅ ተግባር” መኾኑንም አንስተዋል።

 

በመድረኩ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ የፍትሕ ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕዝቡ የሰጠንን ክብር እና ታላቅ አደራ በመቀበል በቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን። 
Next articleማኅበረሰቡ ጤናው ላይ እንዲያተኩር እየተሠራ ነው።