ሕዝቡ የሰጠንን ክብር እና ታላቅ አደራ በመቀበል በቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን። 

4

ሁመራ: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን፤ በቃብትያ ሁመራ ወረዳ ሙሉ እድሳት ሲደረግለት የቆየው የፖሊስ ጽሕፈት ቤት የዞን የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።

 

የአካባቢው ነዋሪዎች የቃብትያ ንዑስ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የውስጥ እድሳት ተደርጎለት ምቹ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ተናግረዋል። በተደረገለት እድሳትም መደሰታቸውን ነው የገለጹት።

 

ሕዝቡ መልካም መንገድ የሚያሳየው መሪ ብቻ ነው የሚፈልገው ያሉት ነዋሪዎቹ አካባቢውን ለማልማት ሁሌም ከመንግሥት ጎን የሚሰለፍ መኾኑን ጠቅሰዋል። ኅብረተሰቡ ይሄንን ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

 

የቃብትያ ንዑስ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ዓለምነው ቸሬ በወረዳው አሥተዳደር እና በከተማው ማኅበረሰብ ትብብር ፖሊሰ ጣቢያው ታድሶ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ተናግረዋል። ፖሊስ ጽሕፈት ቤቱ ከዚህ በፊት ለተገልጋዩ እና ለአገልጋዩ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰዋል።

 

ዛሬ ላይ ከውስጥ እድሳቱ በተጨማሪ ሙሉ አጥር በመገንባት አንድ የጸጥታ ተቋም ሊኖረው የሚገባውን መስፈርት ማሟላቱን ነው ያስረዱት።

 

የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አታላይ ታፈረ ለማገልገል እና ለመገልገል ምቹ ተቋማትን መገንባት ለሀገር ሕልውና መረጋገጥ ዋስትና ነው ብለዋል።

 

ፖሊስ ጽሕፈት ቤቱ ከመታደሱ በፊት አስቸጋሪ እንደነበር አንስተዋል። ይሄንን ሥራ ያከናወኑት አካላት ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል። የተቋሙ መሪዎች በራሳቸው ሃሳብ ጀምረው ፈጽመዋል ነው ያሉት። የተሻለ ተግባራትንም አከናውነዋል፤ ይሄ ደግሞ ለሌሎች ተቋማት ተሞክሮ መኾን የሚችል ነው ብለዋል።

 

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር ወለላው ተገኘ የጽሕፈት ቤቱ መሪዎች ሕዝባቸውን ለማገልገል ቅን እና ቁርጠኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። በአማራር፣ በአደረጃጀት እና ተግባርን በአግባቡ በመፈጸም ረገድ የሚበረታታ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል።

 

“ሕዝቡ ከፖሊስ ጎን ሲኾን በሥራዎቻችን ምን ያህል ውጤታማ መኾን እንደምንችል አረጋግጠናል” ነው ያሉት። እኛም ሕዝቡ የሰጠንን ክብር እና ታላቅ አደራ በመቀበል በቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን ብለዋል።

 

ኅብረተሰቡ እና ፖሊስ አንድ ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ እና የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ተወካይ ጌታቸው ሙሉጌታ ናቸው። ፖሊስ በሚሰጠው አገልግሎት ኅብረተሰቡ ሲረካ እና ኅብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት ያለውን ታላቅ ክብር ማየታቸውን ተናግረዋል።

 

የፖሊስ ተቋማት እና አባላት ለሕዝባቸው ጥቅም ሲቆሙ ሕዝብ የሚሰጣቸውን ፍቅር እና ክብር ማስተዋላቸውንም ገልጸዋል። ይሄንን ተግባር በማጠናከር የዞኑን ሰላም እና ደኅንነት ለማጽናት እየተሠራ ነው ብለዋል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኅብረተሰቡን የመንገድ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
Next articleጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት መፍጠር በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠበቅ ተግባር ነው።