ኅብረተሰቡን የመንገድ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

3

ባሕር ዳር: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የ2017 በጀት ዓመት ምርጥ ፈጻሚዎቹን ሸልሟል። የ2018 በጀት ዓመት ዕቅዱንም አስተዋውቋል።

 

የኤጀንሲው ዋና ሥራ አሥኪያጅ ቀለሙ ሙሉነህ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት ኤጀንሲያቸው ባለፉት ዓመታት በክልሉ ያጋጠመው ችግር ሳይበግረው በርካታ መንገዶችን መገንባቱን ገልጸዋል።

 

ፈተናዎችን በብልሃት እና በትዕግሥት በማለፍ እንዲኹም የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ አድርጓልም ብለዋል።

 

አቶ ቀለሙ ኢትዮጵያ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመፈጸም በኅብረት የምትችል መኾኑን ያሳየችበት ጊዜ በመኾኑ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም ልዩ ተነሳሽነት አለ ብለዋል።

 

ባለፉት ሦሥት ዓመታት በ11 ፕሮጀክቶች 354 ኪሎ ሜትር መንገዶች ተጠናቅቀው ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ኾኗል ነው ያሉት።

 

አቶ ቀለሙ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድንም በተሳካ ኹኔታ ለመፈጸም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል።

 

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ለሀገር ዕድገት የመንገድን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ጠቅሰው ያለፈውን ገምግሞ ለቀጣዩ የመዘጋጀትን አስፈላጊነት ገልጸዋል።

 

በ2017 በጀት ዓመት 1ሺህ 700 ኪሎ ሜትር መንገዶች እና ድልድዮች መሠራታቸውን የገለጹት ዶክተር ጋሻው የገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲም ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

 

በመተባበር በመሠራቱም ከዕቅድ በላይ ተጨማሪ መከናወኑን ጠቁመዋል።

 

ከመንገዶች አኳያ ትልቁ የመንግሥት የመፈጸም አቅም በኤጀንሲው እጅ ነው፤ ችግሮች ሳያሸንፉት ሥራዎቹን አሳክቷል፤ የመፈጸም አቅሙም በየጊዜው እያደገ ነው ብለዋል ዶክተር ጋሻው።

 

የኤጀንሲው መሪዎች እና ሠራተኞች በሰላሙ ጊዜ ከሚሠሩት ሥራ በላይ በተሻለ ትጋት መሥራታቸውን አንስተዋል። ይህንን አቅምም ለቀጣይ የሥራ ዘመን እንደመስፈንጠሪያ አድርጎ መነሳት እንደሚገባ ገልጸዋል።

 

አማራ ክልል ካለበት ችግር ወጥቶ የተሻ ደረጃ እንዲደርስ የ25 ዓመት አሻጋሪ ፍኖተ ካርታ እና የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

 

በመንገድ ዘርፍም ይህንን ዕቅድ በትኩረት ሠርቶ ውጤታማ በመኾን ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

 

ዶክተር ጋሻው ኤጀንሲው በ2018 በጀት ዓመት መንገድ፣ ድልድይ እና ሌሎች ስትራክቸሮች መሥራት እንደሚጠበቅበት እና በበለጠ ተነሳሽነት መሥራት እንደሚገባውም ገልጸዋል።

 

“ፕሮጀክትን ላንጨርስ አንጀምርም” የሚለውን መሪ መልዕክት ይዞ መሥራት እንደሚጠበቅም ነው ያሳሰቡት።

 

በተጀመረው የአሻጋሪ ስትራቴጅክ ዕቅድ እያንዳንዱ ሠራተኛ እና የሥራ ክፍል ኀላፊነቱን አውቆ እና በመተባበር መሥራት እንደሚገባውም አንስተዋል።

 

ፈጥኖ ሥራ በመጀመር እና ፕሮጀክቶችን በወቅታቸው በመፈጸም ከችኮላ ሥራ መላቀቅ እንደሚያስፈልግም ዶክተር ጋሻው ገልጸዋል።

 

ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቀልጣፋ ሥራ እና አገልግሎት፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነትንም የማስፈን አስፈላጊነትን ጠቅሰዋል።

 

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዓለም የቱሪዝም ቀንን ማክበር የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት ያስችላል።
Next articleሕዝቡ የሰጠንን ክብር እና ታላቅ አደራ በመቀበል በቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን።