
አዲስ አበባ: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከአዲስ አበባ ደብረ ብርሃን ያለውን የመንገድ ኮሪደር የሚሸፍን የተሻሻለ የትራፊክ ማስከበር እና የድህረ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ የሙከራ ፕሮጀክት ይፋ ኾኗል።
በመርሐ ግብር ትውውቁ ላይ የተገኙት የመንገድ ደኅንነት እና የመድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ጀማል አባሱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት የትራፊክ አደጋ የሚበዛባቸው ሦሥት ኮሪደሮች ከአዲስ አበባ- አዳማ፣ ከአዲስ አበባ-ፍቼ እና ከሻሸ መኔ-ባቱ ተለይተው ሢሠራባቸው መቆየታቸውን ገልጸው ዛሬ ከአዲስ አበባ ደብረ ብርሃን አራተኛው ኮሪደር ነው ብለዋል።
“ፕሮጀክቶቹ ትንሽ መኪና ያላት ግን ብዙ ሕዝብ በትራፊክ አደጋ የምትጨርስ የሚለውን ትርክት ለመቀየር የምንሠራባቸው ናቸው” ነው ያሉት።
ፕሮጀክቶቹ እንደሆስፒታል የሚያገለግል እና ቀዶ ጥገና ጭምር የሚሰጥበት አንቡላንስ፣ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ የሚያስችል ሀርድ ቶፕ መኪና፣ ለትራፊክ ፖሊሶች ሞተር ሳይክል፣
አልባሳት፣ የነፍስ አድን መሳሪያዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች እና ሌሎችም የተሟሉላቸው ናቸው ብለዋል።
በኮሪደሩ የሚሠሩ የትራፊክ ፖሊሶች፣ የጤና ባለሙያዎች እና የጉልበት ሠራተኞች ሁሉ የተካተቱበት ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ፕሮግራሙን በአግባቡ በመተግበር ከአደጋ በኋላ የሚከሰትን ሞት 50 በመቶ መቀነስ እንደሚቻልም ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ እና የአማራ ክልል የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ይህ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት እውን እንዲኾን የተባበሩ አካላትን አመሥግነዋል።
ክልሉ ለቀጣይ 25 ዓመታት የሚያገለግል ስልታዊ ዕቅድ ማዘጋጀቱን አውስተው የትራንስፖርት መሠረተ ልማትን ማስፋት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ማድረግ አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
የትራንስፖርት ዘርፉን ማስፋት እና ማዘመን ክልሉ ላቀዳቸው ዕቅዶች ስኬት አጋዥ ይኾናል ብለዋል።
የተሻሻለ የትራፊክ ማስከበር እና የድህረ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ የሙከራ ፕሮጀክት ስኬታማ እንዲኾን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። የክልሉ መንግሥትም ያላሰለሰ ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ነው ያሉት።
የተሻሻለ የትራፊክ ማስከበር እና የድህረ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ የሙከራ ፕሮጀክት ለአንድ ዓመት የሚቆይ እንደኾነም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!