
ደባርቅ: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ሂደት አጋዥ የኾኑ የተለያዩ ተግባራትን በንቃት ሲያከናውን መቆየታቸውን ተመላክቷል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሰብል ልማት ሥራዎችን በትኩረት ለመተግበር መታቀዱም ተገልጿል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አዳነ በ2017 በጀት ዓመት በመስኖ ሰብል ልማት፣ በግብዓት ሥርጭት እና በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ አበረታች ተግባራት ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በሰው ኃይል ስምሪት እና ሕጋዊ ተጠያቂነትን በማስፈን በኩል ሊሻሻሉ የሚገቡ ክፍተቶች መለየታቸውንም ገልጸዋል። በቀጣይም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ የደን ልማት እና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎችን በትኩረት ለመሥራት መታቀዱን አንስተዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሰብል፣ የአትክልት እና ፍራ ፍሬ ሥራዎችን ለማከናወን በትኩረት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በግብርና ዘርፍ የላቀ አፈጻጸም ካስመዘገቡ ወረዳዎች መካከል የበየዳ ወረዳ እና ጃናሞራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ይገኙበታል።
የበየዳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረ ሕይዎት በላይነህ በተፈጥሮ ሃብት እና ተፋሰስ ልማት ሥራ አበረታች ተግባራት ማከናዎናቸውን ተናግረዋል።
የተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎችን በሥነ ሕይወታዊ ዘዴ በማጠናከር እና ዘላቂነታቸውን በማረጋገጥ በኩል የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደ ነበር አብራርተዋል።
የጃናሞራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሷሊህ ሃሰን ማኅበረሰብ አቀፍ አደረጃጀቶችን በመፍጠር እና አደረጃጀቶችን በማጠናከር ረገድ መልካም ተግባራት እንደተከናወኑ ገልጸዋል።
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የአፈር ለምነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት መከናዎናቸውንም ጠቅሰዋል። በቀጣይም “የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያስችሉ የተሻሻሉ ተግባራትን ለማከናዎን ትኩረት ይሰጣል” ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!