
ባሕር ዳር: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ለመማር ፍላጎት አለኝ የሚለው ተማሪ ዮሐንስ ዋለ ነው፡፡
በጸጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጠበትን ትምህርት ፍለጋ ከተወለደበት አካባቢ ወደ ደብረ ታቦር ተጉዟል፡፡ እንደ ቤት ባይመችም ለትምህርት እና ለዓላማው መሳካት አስፈላጊውን መስዋዕትነት እየከፈለ ነው፡፡ ከ7ኛ ወደ 8ኛ ክፍልም አንደኛ ደረጃን ይዞ አልፏል፡፡ ህልሙም ሩቅ ነው።
ይሁን እንጂ በቤቱም ኾነ በትምህርት ቤት እውቀት ለመቅሰም ምቹ ኹኔታዎች እንደሌሉ አንስቷል፡፡ ነገር ግን በደብረ ታቦር ከተማ እየተገነባ ያለውን አዳሪ ትምህርት ቤት በሰማ ጊዜ እድሉን ለማግኘት በተስፋ እየተጠባበኩ ነው አለን።
ቴክኖሎጂን ጨምሮ የትምህርት ቁሳቁስ፣ ሙሉ ጊዜ፣ የምግብ እና ሌሎች ወጪዎች እንዲኹም እውቀት እና ክህሎት ያላቸው መምህራንን በማግኘት ህልሙን እውን ለማድረግ የአዳሪ ትምህርት ቤቱን ግንባታ መጠናቀቅ በጉጉት እየተጠባበቀ ነው።
ተማሪ እዩኤል ጎሹ ደግሞ በደሴ የይሁኔ ወልዱ አዳሪ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ለመማር ተፈትኖ ነው ያለፈው። በዚህም የዕድሉ ተጠቃሚ ኾኗል። በዩኒቨርሲቲም ህክምና የማጥናት ህልም አለው።
በአዳሪ ትምህርት ቤት መማር በመደበኛ ትምህርት ቤት ከመማር የበለጠ ምቹ እና ብቁ እንደሚያደርግ ገልጿል። የትምህርት ቁሳቁስ መሟላት፣ ሙሉ ጊዜን ለትምህርት ማዋል፣ ከሚያዘናጉ ነገሮች ነጻ መኾን፣ በውድድር መንፈስ እና በብቁ መምህራን መማር ተጠቃሽ መኾናቸውን አንስቷል።
በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ከ85 አማካይ በታች ውጤት ላላቸው ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግ ነው ተማሪ ኢዩኤል የገለጸው።
ምጡቅ አዕምሮ እና የተሻለ ውጤት ያላቸው ተማሪዎችን በአዳሪ ትምህርት ቤት በማስተማር በእውቀት፣ ክህሎት እና ሥነ ምግባር በማነጽ ሀገርን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተወዳዳሪ ለማድረግ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት እየተሠራ ነው፡፡
ከነዚህ ውስጥም በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እየተገነባ ያለው የአዳሪ ትምህርት ቤት አንዱ ነው፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ ግንባታው በመጋቢት 2016 ዓ.ም ተጀምሮ በ2018 ለማጠናቀቅም እቅድ መያዙን ነገሩን።
ለሁለት ተቋራጮች ተከፋፍሎ የተሰጠው የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ የመማሪያ፣ የማደሪያ፣ የመመገቢያ፣ የቤተ መጻሕፍት እና ሌሎችንም ይዟል፡፡ ግንባታው ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር እስከ 400 ተማሪ ተቀብሎ እንደሚያስተምር ነው ኀላፊው የገለጹት፡፡
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሲቪል ምህንድስና ዳይሬክተር መሀንዲስ ሚካኤል ንብረት በክልሉ ውስጥ የሚከናወኑ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ክትትል እየተደረገላቸው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በሁለት ተቋራጮች የሚፈጸመው የደብረ ታቦሩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባትም የአንደኛው ተቋራጭ 58 በመቶ እና ሁለተኛው ደግሞ 74 በመቶ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
እስከ የካቲት 2018 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅም እየተሠራ መኾኑንም ነግረውናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!