
ባሕር ዳር: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ እየተገነቡ ከሚገኙ ሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል በወለህ እየተገነባ የሚገኘው የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ አንደኛው ነው።
ግንባታውን በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ታስቦ የካቲት 2016 ዓ.ም ወደ ሥራ መገባቱን መዘገባችን ይታወሳል። ትምህርት ቤቱም በክልሉ መንግሥት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል። ግንባታው በሁለት ተቋራጮች ተከፍሎ በመከናወን ላይ ይገኛል።

የወለህ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ማህሌት ቅባቴ እንደገለጸችው ባለፉት የትምህርት ዓመታት በእንጨት እና በጭቃ የተሠሩ ክፍሎች ከግብዓት አለመሟላት ጋር ተዳምሮ የመማር ማስተማር ሂደቱን ፈታኝ አድርጎት ቆይቷል። ይህንን ችግር በመቋቋም አንደኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋንም ነው የተናገረችው።
በአካባቢው እየተገነባ በሚገኘው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የመማር ዕድሉን ለማግኘትም የሌሊት ጊዜዋን ጭምር በንባብ እያሳለፈች መኾኗን ገልጻለች።
ተማሪ ማህሌት ቅባቴ ደረጃውን በጠበቀ ትምህርት ቤት ተምራ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መቀላቀል ሕልሟ ነው።
የወለህ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የልዩ ፍላጎት መምህር አማረ አሰፋ እንዳሉት የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ መገንባት የተማሪዎችን የትምህርት ፍላጎት ይበልጥ ያነሳሳ ነው።
ተማሪዎችም የተሻለ ውጤት አምጥተው የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ከአሁኑ የሥነ ልቦና ግንባታ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ከሥነ ልቦና ግንባታ ባለፈ በመደበኛ እና በትርፍ ጊዜ ጭምር የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሠጠ መኾኑን ገልጸዋል።
አዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ከሚያስጠብቁ ተቋማት መካከል በመኾናቸው የተጀመሩ ግንባታዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ጠይቀዋል።
የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ እንየው እውነቱ አሁን ላይ የግንባታ ሂደቱ 75 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። የግንባታው የመጨረሻ ሥራ ላይ መኾኑንም ተናግረዋል። እስከ ጥር/2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሲቪል ምሕንድስና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሚካኤል ንብረት እንደተናገሩት የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤትን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል። ተቋራጮችም ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዲሠሩ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!