የመጣው አንጻራዊ ሰላም በግብር አሠባሠቡ ላይ አወንታዊ ለውጥ እያመጣ ነው።

9
ባሕር ዳር: መስከረም 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን ገቢዎች መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና ከ25 ዓመቱ የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድን መነሻ ያደረገ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ነው።
በዕለቱ የተገኙት የሰሜን ጎጃም ዞን ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ጌታዬ ሙጨ ግብር የመንግሥትን ገቢ ከፍ የሚያደርግ እና የመሠረተ ልማት ፍላጎትን ምላሽ መስጠት የሚያስችል መሠረታዊ ነገር ነው ብለዋል። የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግም ሁነኛ ተግባር እንደኾነ ነው የገለጹት።
ግብርን መሠብሠብ ለመንግሥት የመንግሥትነት ምልክት ሲኾን በአንጻሩ ለግብር ከፋዩ ደግሞ የሥልጣኔ ምልክት ማሳያ ነው ብለዋል። በ2017 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሠብሠብ መቻሉን ኀላፊው ገልጸዋል።
ይህም ከታቀደው 75 ነጥብ 5 በመቶ የሚኾነውን መፈጸም እንደተቻለ ነው የተናገሩት። ከነበረው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የተሠራው ተግባር ጥሩ የሚባል ሲኾን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ መኾኑን ነው የገለጹት። የመጣው አንጻራዊ ሰላም በግብር አሠባሠቡ ላይ አወንታዊ ለውጥ እንዳመጣ ነው የተናገሩት።
ለ2018 በጀት ዓመትም 2 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዷል ብለዋል። በመድረኩ በገቢ አሠባሠቡ የተሻለ ለፈጸሙ ወረዳዎች እና ምስጉን ግብር ከፋዮች እውቅና እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ840 ሺህ ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
Next articleሕዳሴ የመቻል ማሳያ ነው።