
ደብረ ብረሃን: መስከረም 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ገቢዎች መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት የንቅናቄ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ነው።
በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠብ መቻሉን የተናገሩት የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ቀለም ተስፋዬ ናቸው።
በተያዘው የ2018 በጀት ዓመትም 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል። እስካሁን በተሠራው ሥራም የዕቅዱን 15 በመቶ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።
የግብር ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ታክስ የማዘመን ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤሊያስ አበበ ግብርን በመሠብሠብ ለታለመለት አላማ እንዲውል መሥራት የጠንካራ መንግሥት መገለጫ እንደኾነ ተናግረዋል። ዞኑ ያለውን እምቅ ሃብት ለይቶ ወደ ሥራ በመገባቱ ገቢ የመሠብሠብ አቅሙን ማሳደግ ችሏል ነው ያሉት።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ ግብር የመንግሥትን ሥራዎች ማሳለጫ በመኾን የሕዝብ የልማት ጥያቄዎችን የሚመልስ የኢኮኖሚ መሠረት ነው ብለዋል።
በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሠብሠብ የዕቅዱን 84 በመቶ መፈጸም እንደተቻለ ተናግረዋል። ፈተናዎችን በመቋቋም በተሠራው ሥራ እና በግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ቀና ትብብር ገቢ መሠብሠብ መቻሉን ነው የገለጹት።
በክልሉ ከሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚ አንጻር የሚሠበሠበው ገቢ በቂ ባለመኾኑ በቀጣይ ጊዜያት አቅምን አሟጦ ለመሠብሠብ መታቀዱን ገልጸዋል። በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት በአማራ ክልል ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!