
ደብረ ማርቆስ: መስከረም 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራን በንቅናቄ ለማስጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በግጭቱ ምክንያት በዞኑ በርካታ ተማሪዎች ከመማር ማስተማር ተግባር ውጭ በመኾናቸው በሕጻናት ራዕይ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡
ከችግሩ ለመውጣት ኅብረተሰቡ፣ የትምህርት ባለሙያው፣ የትምህርት መሪዎች እና ባለድርሻ አካሉ ሁሉ ኀላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።
የትምህርት ዘርፍ ላይ የገጠመን ችግር ሀገር እና ትውልድን ለውድቀት የሚዳርግ በመኾኑ ሁሉም ባለድርሻ እና አጋር አካል በጋራ ሊሠራበት ይገባል ነው ያሉት።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ በዞኑ ከ790 ሺህ በላይ ሕጻናትን ለማስተማር ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። የሕጻናት ራዕይ እንዳይጨልም ለትምህርት ዘርፉ መሥራት የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይኾን ግዴታም ጭምር መኾኑን አስገንዝበዋል።
የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና የ2018 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ በንቅናቄ ለማስጀመር በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!