
ባሕር ዳር: መስከረም 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓላትን ተዝናንቶ እና ተደስቶ ማክበር ባይከፋም ከአቅም በላይ ለመደገስ እና ለመልበስ ጥሪትን ማሟጠጥ ብሎም አላስፈላጊ ብድር መግባት አሁን ድረስ ያላሻሻልነው ትክክል ያልኾነ ልማድ ነው።
ለአንድ ቀን ወይም ለሰሞንኛ ድግስ እና ጌጥ ብሎ የወርን ብሎም የዓመት ጥሪት አሟጦ መደገስ እና መልበስ አለማስተዋል ነው። እንደ ቤት መኖር እየተቻለ ጎረቤት ለመምሰል የሚደረግ መፍጨርጨርም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።
በግ ማረድ ባይቻል ዶሮ፣ እሱም ካልኾነ ሽሮ በልቶ ማደር ማንን ገደለ? ከሰው ላለማነስ በሚል መስሎ አዳሪነት ከአቅም በላይ ማውጣት ወይም መበደር በዓሉ ሲያልፍ ለችግር ያጋልጣል።
አንዳንዶች በበዓል ልጆቼን እንዳይከፋቸው በሚል ሽፋን የወራት አስቤዛቸውን ለአንድ ቀን በዓል ምግብ፣ መጠጥ እና አልባሳት ማዋል አሁንም ድረስ የሚስተዋል ነው።
ተበድሮ መደገስ እና መልበስ ከበዓሉ በኋላ ለመኮሰስ እንደሚያጋልጥም እያወቁ ለምን በአቅም እንደማይኖሩ ሳስበው የኾነ ያላወቅነው ጎጅ ልምድ እንደተጫነን አስባለሁ።
በነሐሴ ወር ፆም የሚደገስ “አድርሽኝ” በሚል የሚጠራ ድግስ፣ የዘመን መለወጫ፣ የመስቀል፣ ዐቢይ ጾም እስኪገባ ድረስ ያሉት በዓላት፣ ልደት፣ ክርስትና፣ ቀለበት፣ ሰርግ እና ሌሎችም የሚደገስባቸው እና ያለ አቅም ገንዘብ የሚያስወጡ ሁነቶቻችን ናቸው። ጓደኛሞች በአንድ ላይ ሰብሰብ ብለው ለመዝናናት ድንገት ገንዘብ የሚያዋጡበት ልማድም ተጠቃሽ ነው።
በዓላቶቻችን ከሰው ላለማነስ እና እንደ ሀገር ለመኾን ከአቅም በላይም ወጭ የሚወጣባቸው ልምድ አቅምን ያገናዘበ መኾን እንዳለባቸው አምናለሁ።
ሃይማኖታዊም ይሁኑ ባሕላዊ በዓላቶቹን ማክበር እና በጋራ መዋል ጠቃሚ በመኾኑ ሊቀጥሉ ይገባል፤ ችግሩ ግን ያለ አቅም ወጭ ማብዛቱ ነው። ለበዓላት በምንሰጠው ከፍተኛ ግምት ለመደሰት እና ከሌላው ላለማነስ ከፍተኛ ወጭ እናወጣለን።
ምግብ፣ መጠጥ፣ አልባሳት የቤት ቁሳቁስ ሳይቀር ለበዓል አዲስ መግዛት ካልተቻለም አጥቦና አድሶ መጠቀም የግድ ነው። ስጦታም ሌላው የበዓላቶቻችን አካላት ናቸው። በዚያ ላይ በይሉኝታ እና ሌላውን ለማስደሰት ሲባል ከልክ በላይ ይከወናሉ።
ይህ ለዘመናት የዘለቀ በዓላትን አምሮ፣ ደምቆ፣ ተደስቶ ለማክበር ከአቅም በላይ የመደገስ እና ሃብት የማፍሰስ ባሕል ዛሬ የኑሮ ውድነት ባለበት ዘመንም አልቀረም። ያውም በብዙ ወጭ ያከበርነው በዓል ካለፈ በኋላ የሚያመጣውን ጣጣ እያወቅነው።
በርካቶቻችን ያለ አቅም መደገስ እና የመልበስን አላስፈላጊነት በአንደበታችን እየተናገርን በተግባር ግን አልተሻሻልንም ባይ ነኝ። ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስን የሚተርቱም ጥቂት አይደሉም።
በርካቶቻችን ያለ አቅማችን ለበዓላት እናወጣለን ለዚያውም ተበድረን ጭምር። ስንበደር ተሳቅቀን፤ ብድሩን እስክንመልስ ተሳቅቀን፤ ወጭው ኑሯችን አዛብቶት፣ ለችግር፣ ለጸጸት እና ለንዴት ዳርጎን ሲያልፍም ብዙ ጊዜ ታዝቤያለሁ።
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር ለችግር የሚዳርገን እና መታረም ያለበት በዓል ማክበራችን ሳይኾን ወጭዎቻችን በአቅም እና በዕቅድ አለመኾናቸው ነው።
ዘይት፣ ስኳር፣ ቡና፣ ለልጆች ልብስ እና መጫዎቻ ወዘተረፈ ለአንድ ሠርቶ አዳሪ ደሀ የዓመት ዕዳ ነው የሚኾኑት። ለእገሌ ሰጥቼ ለእገሌስ የሚሉት ዓይነትን ይሉኝታ አውልቆ መጣል ያስፈልጋል። አለበለዚያ በቀናት ለሚያልፍ በዓል የወራትን እዳ ሊያመጣ ይችላል ነው ምክሬ።
መፍትሔው በዓላትንም ኾነ መሰል ወጭ ጠያቂ ሁነቶች ላይ በአቅም መሳተፍ ነው እላለሁ። ይሉኝታ እና መስሎ ማደርን መቀነስ፤ ቢገኝ ተበልቶ፣ ተጠጥቶ፣ ተለብሶ፣ ተስቆ፤ ካልተገኘም ከዕዳ ነጻ ኾኖ ሳይሳቀቁ መኖር ትልቅ ዘዴ ነው።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!