
ባሕር ዳር: መስከረም 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደርግ መንግሥት የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት በያዝነው ወር መስከረም 1966 ዓ.ም አስወግዶ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ሀገርን የሚያሳድጓት ምሁራን ናቸው ብሎ በማመን በዙሪያው ምሁራንን ነበር ማሠባሠብ የጀመረው።
በርግጥ የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣው በወታደራዊ መንገድ ቢኾንም ነገር ግን በአብዛኛው በበትረመንግሥቱ ዙሪያ የተሠባሠቡት ወደ ውጭ ሄደው የተማሩም ነበሩ።
በትምህርት ላይ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት የሚታማ አልነበረም። በርካቶች ትምህርት እንዲቀስሙ ከሀገር ውስጥ እስከውጭ በርካታ ጥረት አድርጓል ማለት ይቻላል።
ከንጉሡ ሥርዓት ስለትምህርት ልምድ የቀሰመው ደርግ ሀገር የምታድገው ሕዝቡ ሲማር ነው ብሎ በማመኑ ከገጠር እስከ ከተማ ዜጎች እንዲማሩ የመሠረተ ትምህርት በማስፋፋት ትልቅ ጥረት አድርጓል።
በተለይም የገጠሩ ማኅበረሰብ ቀለምን ከተግባር ጋር አጣምሮ እንዲማር በዚህ ሳምንት መስከረም 05/1975 ዓ.ም ከዛሬ 43 ዓመት በፊት በያዝነው ሳምንት በባሌ አጋርፋ የገበሬዎች ሁለገብ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተመርቆ የተከፈተበት አንዱ ማሳያ ነው።
ትምህርት ለሰፊው ሕዝብ ደረጃ በደረጃ እንዲዳረስ፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂም እንዲዳብር የታለመውን ግብ ተግባራዊ ለማድረግ ይህንን የገበሬዎች ሁለገብ ማሠልጠኛ ተቋም መርቀው መክፈታቸውን መናገራቸውን ታሪክ ይነግረናል። መንግሥቱ ኃይለማርያም በዚሁ ምረቃ ላይም “ሀገርን የሚያሳድጓት ቀለምን ያወቁ ናቸው” ማለታቸውን ታሪክ ከትቦታል። ምንጭ፦ በሪዱልፍ ሞልቫር የተጻፈው ዘብላክ ላዮን መጽሐፍ

አርቲስት ሲራክ ታደሰ በወሎ ዋድላ ደላንታ ልዩ ስሙ ወገል ጤና በተባለ ሥፍራ በ1939 ዓ.ም ነው የተወለደው። አርቲስቱ ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ በሀገሩ ባሕል መሠረት ዜማ እና ቅኔ እንዲሁም ድጓና ፆመ ድጓ ከአቋቋም ጋር የቤተክርስቲያኒቱ አብነት የኾነውን ያሬዳዊ ዝማሬ ተምሮ ጨርሷል።
ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በግቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያ ከማገልገሉም በላይ በሊቃውንት ጉባኤ አባልነት ሢሠራም ቆይቷል።
ምድር ጦር የሙዚቃ ክፍልን መቀላቀል የቻለው አርቲስቱ በቲያትር ተዋናይነት፣ በግጥምና ዜማ ደራሲነት ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1969 ዓ.ም ድረስ ካገለገለ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ተመርጦ ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ጡረታ እስከወጣበት 1997 ዓ.ም ድረስ በግጥም፣ በዜማ ደራሲነት እና አጫጭር ልብወለዶችን በመጻፍ አገልግሏል።
በተለይ ለጥላሁን ገሠሠ፣ ማሕሙድ አሕመድ፣ ታምራት ሞላ፣ ምኒሊክ ወስናቸው፣ መልካሙ ተበጄ፣ ለገሠ ቀናው፣ ዓባይ በለጠ እና ለሌሎችም ታዋቂ የሀገሪቱ አርቲስቶች ትውልዱ የማይሰለቻቸውን የዘፈን እና የግጥም ዜማዎች በመድረስ ለሕዝብ እንዲሰማ አብቅቷል።
አርቲስት ሲራክ ታደሰ በትወናው ዘርፍ አሉላ አባ ነጋ፣ ሀሁ በ6 ወር፣ የአመፃ ልጆች፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ነፃ ወንጀለኞች፣ መርዛማ ጥላ እና በተለይም ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈበት በአምታታው በከተማ ጉልሽ ኾኖ የተጫወተበት ገፀ-ባሕሪ ይታወሳል።
አርቲስት ሲራክ ታደሰ በወቅቱ በርካታ ተመልካቾችን በሚስቡ የፊልም ጥበብ ውስጥ በመሥራት አድናቆትን ያተረፈ ሲኾን ብዙ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ድራማዎችንም ተጫውቷል።
በተጨማሪም አርቲስቱ ባለው ከፍተኛ የተዋናይነት ችሎታ እና ተወዳጅነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ለ5 ዓመታት የጡረታ ዘመኑ እንዲራዘምለት የተደረገ ምርጥ የጥበብ ፈርጥ ነበር።
ይህ ድንቅ አርቲስት በዚህ ሳምንት መስከረም 08/2001 ዓ.ም በ63 ዓመቱ ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው። ምንጭ፦ በፋንታሁን እንግዳ የተጻፈው ታሪካዊ መዝገበ ሰብ መጽሐፍ

እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን በዚህ ሳምንት መስከረም 15/2007 ነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዴሞክራሲ ለሰው ልጅ ወሳኝ መኾኑን አውቆ በቁጥር 62/7 በተሰኘ ድንጋጌ የዲሞክራሲ ቀን እንዲከበር የወሰነው።
የዴሞክራሲ ቀን በዚህ ዓመትም በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ችሏል። በተለይም በዚህ ዓመት በተከበረው በዚህ በዓል የዴሞክራሲ እሴቶች በመረጃ ማዛባት፣ መከፋፈል እና የዜጎችን ተሳትፎ በመገደብ ላይ ጥቃት እየደረሰባቸው የሚገኙ ዜጎች እንዲታሰቡ ነው የተደረገው።
ዴሞክራሲ ለሰው ልጅ ጠቃሚ መኾኑን በመረዳት የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት የዴሞክራሲ ፈንድ (UNDEF) 20ኛ ዓመቱን ሲደፍን በዓለም ላይ ዴሞክራሲ እንዲሰፋ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
“ከድምጽ ወደ ተግባር” በሚል በዚህ ዓመት የተከበረው የዴሞክራሲ ቀንም ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ያሳሰበም ኾኗል።
የዴሞክራሲ ቀን መከበሩ በዓለም ዙሪያ የሲቪል ማኅበራትን፣ ተቋማትን እና የሰብዓዊ መብት መከበር እንዲጠናከር ከፍተኛ እገዛም አድርጓል። የዴሞክራሲ መርሆች የሰላም እና የአካታችነት ኀይል እንዲኾኑም ማድረግ የተቻለበት ነው። ምንጭ፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረገጽ

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየዓመቱ መስከረም 21 ልክ በዛሬው ቀን የሚከበረው የዓለም የሰላም ቀን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1981 ዓ.ም በሙሉ ድምጽ የጸደቀ ዓለማቀፍ ቀን ነው። ይህ ቀን ለሁሉም የዓለም ሕዝብ፣ ልዩነቶችን በመተው ለሰላም ቅድሚያ ለመስጠት እና የሰላም ባሕልን ለመገንባት ቃል የሚገባበት የጋራ ቀን ነው።
የ2025 የዘንድሮው የሰላም ቀን መሪ መልዕክትም “ለሰላማዊ ዓለም አሁኑኑ እንሥራ” የሚል ሲኾን ይህ መሪ መልዕክት በተለይ በወቅታዊው ዓለም አቀፋዊ አለመረጋጋት፣ ግጭት እና ጥርጣሬ ውስጥ ለሰላም የሚኾን ተጨባጭ ተግባር መፈጸም ወሳኝ መኾኑን ያሳያል።
ሁሉም ሰው ይህን ቀን ሲያከብር ታዲያ ለሰላም አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚባሉ ጉዳዮችን በመፈጸም ሊኾንም ይገባል።
በተለይም ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ትክክለኛ መረጃዎችን በማጣራት ብቻ መለጠፍ፣ በማኅበረሰብ ውስጥ ልዩነትን መቀበል እና በአድሎአዊ ንግግሮች ላይ መዝመት፣ በየዕለቱ ከጥላቻ፣ ከጥቃት፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ከኢ ፍትሐዊነት ጋር መታገል ያስፈልጋል። ምንጭ፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረገጽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!