
ደብረብርሃን: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የ2018 የትምህርት ዘመንን ውጤታማ ለማድረግ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ መምሪያ ድረስ ካሉ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ የሕጻናትን እና የታዳጊዎችን የመማር ዕድል ዕውን ለማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ የሚጠበቅ ወቅታዊ ተልዕኮ መኾኑን ገልጸዋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን በከተማው 12 ትምህርት ቤቶች ማስተማር አለመቻላቸውን ያስታወሱት ኀላፊዋ ትምህርት ላይ ያለው ብክነት የትኛውንም ወገን ሊያሳስበው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ችግሩን በልኩ ተረድቶ የመማር ዕድሉ የተነፈጋቸውን ሕጻናት ዳግም ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ሥራው በተሟላ ሁኔታ መፈጸም እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የትምህርት ተቋማት ያለባቸውን ችግር ተከታትሎ አስቻይ የመማር ማስተማር ከባቢ ለመፍጠር በቀጣይ በቅርበት መደገፍ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በየትኛውም ፈተና ውስጥ ቢኾን የትምህርት ሥራ መቋረጥ የሌለበት ሰብዓዊ ልማት መኾኑን ገልጸዋል።
ለየትኛውም ችግር እጅ ባለመስጠት በየደረጃው ያሉ መሪዎች እና ፈጻሚ አካላት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ማስቻል የዚህ ዓመት ቁልፍ ተልዕኮ መኾኑንም ተናግረዋል።
የትውልድ ክፍተት ተፈጥሮ ተወቃሽ ላለመኾን ለትምህርት ሽፋን መረጋገጥ የድርሻችንን በአግባቡ ማበርከት አለብን ብለዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የቀበሌ፣ የክፍለ ከተማ እና መምሪያ ባድርሻ አካላትም በትምህርት ዘመኑ ሁሉም የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሥራዎችን ማከናወን እንዲችሉ ተገቢ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ አበበች የኋላሸት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!