
ጎንደር: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከክልሉ እና ከፌዴራል መንግሥት እንዲሁም ከኅብረተሰቡ ጋር በጋራ በመኾን ያስገነባቸውን የተለያዩ ፕሮጀክቶች እያስመረቀ ነው።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች እንዲሁም ተጋባዥ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአይራ 2ኛ ደረጃ የግብይት ማዕከልን፣ የስማርት ሲቲ ማስተባበሪያ ማዕከልን እና የጅንዓድ ፒያሳ መዝናኛ ማዕከልን መርቀዋል።
በጎንደር ከተማ የተገነቡት የመሠረተ ልማት ሥራዎች ካለፉት ዓመታት በላቀ ሁኔታ የከተማዋን እንቅስቃሴ ያነቃቁ መኾናቸውን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አንስተዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ የከተማዋን ሕዝብ እና ደረጃ የሚመጥኑ መኾናቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ አብራርተዋል። በከተማዋ በየጊዜው የተሠሩ አዳዲስ የልማት ሥራዎች ውጤታማ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የገበያ ማዕከሉ ሻጭ እና ገዥን በማገናኘት ያልተገባ ትርፍን ለማግኘት የሚጥሩ አካላትን እንደሚያርምም ገልጸዋል።
እሴትን የጨመሩ ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ያስችላልም ብለዋል።
አርሶ አደሮች የሚያገኙትን ጥቅም የሚያስቀሩ የግብይት ሰንሰለቶችን በማሳጠር የሚገባቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ያደርጋልም ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።
የተመረቁ ማዕከላት የክልሉን እና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያሻሻሉ መኾናቸውንም አመላክተዋል።
የክልሉ መንግሥት መሠል ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉ እንደሚያግዝም ተገልጿል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር መሠል ኘሮጀክቶችን በማፋጠን የአካባቢውን ገጽታ በሚመጥን መልኩ መሥራት አለበት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከተማ አሥተዳደሩ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ቦታዎችን ሕጋዊ መስመር በማስያዝ ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ እንደሚገባውም ገልጸዋል።
ከተማዋ በጥቂት መሪዎች ብቻ ሳይኾን በብዙ መሪዎች ድምር ውጤት መልማት እንዳለባት እና ገቢን በመሠብሠብ ብልሹ አሠራርን ማረም እንደሚገባም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦መሠረት ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!