
ጎንደር: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የተገነባውን የአይራ የግብይት ማዕከልን መርቀው ለአምራች እና ሸማቾች ክፍት አድርገዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የተጠናቀቀው የገበያ ማዕከል አምራች እና ተጠቃሚውን በአንድ ቦታ በማገናኘት ዕለት ከዕለት የሚደረገውን የግብይት ሥርዓት እንደሚያዘምን ገልጸዋል።
ጎንደር ለንግድ ሥራ ቀዳሚ ከተማ እንደነበረች ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ባላት አቅም ልክ ሳትለማ መቆየቷን ጠቅሰዋል።
እንደዚህ አይነት የግብይት ማዕከላት መሠራታቸው ደግሞ ለከተማው ዕድገትም ኾነ ለነዋሪዎቿ ተጠቃሚነት ዕድል የፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ በክልሉ መንግሥት እና በከተማ አሥተዳደሩ ቅንጅት በ162 ሚሊዮን ብር ወጭ መገንባቱ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ንግድ የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በመኾኑ የማዕከላት መገንባት ሥርዓቱን ያዘምነዋል ብለዋል።
በሌሎች ሰባት የከተማ አሥተዳደሮችም ተመሳሳይ የግብይት ማዕከላት እየተገነቡ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የግብይት ማዕከላቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን ረዥም የግብይት ሰንሰለትን በማስቀረት ሸማቹ ላይ ያልተገባ ጭማሪን እንደሚያስቀርም አብራርተዋል።
ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ አድርጓል ነው ያሉት።
ዘጋቢ :- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!