ከተማን የማዘመን ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

4

ወልድያ: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎”አርቆ ማየት አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልዕክት የወልድያ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት እና የፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ እየተካሄደ ነው።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ ገብሬ የ2018 በጀት ዓመት የ25 ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የመጀመሪያ ምዕራፍ በመኾኑ ለዕቅዱ ስኬት ጠንካራ መሠረት መጣል ያስፈልጋል ብለዋል።

በመኾኑም የእያንዳንዷን ሰዓት፣ ዕለት እና ወር ተግባር በአምስት እጥፍ ከፍ አድርጎ መሥራት የመሪዎች እና የመንግሥት ሠራተኛው ቁልፍ ተግባር ሊኾን እንደሚገባም ተናግረዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዝናቡ ሰጠ ከክልሉ የ25 ዓመት ዕቅድ አኳያ ከተማዋን በማዘመን ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ዮሐንስ ገበያው በበኩላቸው የከተማዋን የኢንዱስትሪ ፍሰት በማፋጠን የሥራ ዕድል የመፍጠር እና የከተማዋን ገቢ የማሳደግ ርዕይ ተይዞ እንደሚሠራም ነው ያብራሩት።

የወልድያ ከተማ አሥረተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ መሪዎች ዕደገትን ለማሳለጥ ቁልፍ በመኾናቸው ወልድያ ከተማን የማዘመን እና የኢንዱስትሪ ከተማ እንድትኾን ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው ብለዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ፓርቲው በሕዝቡ ተመራጭ እንዲኾን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የኅብረተሰቡን እርካታ በተገቢው መንገድ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

መሪዎች ከከተማዋ ዕድገት ጀምሮ እስከ ሀገር ልማት እና ብልጽግና ቁርጠኛ ኾነው እንዲሠሩም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር ) በ2017 በጀት ዓመት እንደ ክልል በችግር ውስጥ ተኾኖም ከሕዝብ ጋር የሚያቆራኙ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደርም ይሠራሉ ተብለው የማይታሰቡ ልማቶችን በከተማዋ በፍጥነት ሠርቷል፤ ይህንንም በጥራት እና በቅልጥፍና በመሥራት ማስቀጠል ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
Next articleየገበያ ማዕከል መገንባት የንግድ ሥርዓቱን ያዘምነዋል።