
ባሕር ዳር: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ልማት እና ጸረ ወባ ማኅበር “ወባን በእኛ ሃብት፣ በእኛ ዕውቀት እና ገንዘብ አናጠፋለን” በሚል መሪ መልዕክት 27ኛ የምሥረታ ዓመቱን አክብሯል። ማኅበሩ ያከናወናቸው ሥራዎችም በዕለቱ ቀርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የወባ በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ደግም የታዳጊ ሀገራት የማኅበረሰብ ችግር ኾኖ ዘልቋል ብለዋል።
አሁን ላይም በአማራ ክልል የማኅበረሰብ የጤና ችግር ኾኖ ቀጥሏል ነው ያሉት።ባለፉት ዓመታት ወባን ለመከላከል በተሠጠው ትኩረት ማኅበሩ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ጭምር ግብዓት በማቅረብ ኀላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን ገልጸዋል።
ማኅበሩ ወባን ከመከላከል ባለፈ ሌሎች የጤና ተግባራትን በማከናወን የመንግሥትን ክፍተቶች የመሙላት ሥራ መሥራቱንም አንስተዋል።
የማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናት እና ምርምር፣ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ እና የመንግሥት ክፍተቶችን በማሳየት የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ባለፉት ዓመታት ወባ ላይ በተሠራው ሥራ ከአስሩ ለሞት አጋላጭ ከኾኑ በሽታዎች ውጭ ማድረግ ቢቻልም ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን በሽታው እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ2 ሚሊዮን በላይ የወባ ሕሙማንን ማከም መቻሉንም በማሳያነት አንስተዋል።
በሽታውን “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ” በሚል መልዕክት በንቅናቄ የመከላከል ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። በመከላከል ተግባሩ ደግሞ የማኅበሩ ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ነው ያነሱት። በተለይም ደግሞ አስቸጋሪ በሚባሉ ቦታዎች ጭምር ግብዓት በማድረስ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ ሀገር በቀል ማኅበር መኾኑንም ገልጸዋል።
የጤና ልማት እና ጸረ ወባ ማኅበር ዳይሬክተር አበረ ምህረቴ ማኅበሩ ባለፉት 27 ዓመታት በክልሉ እና በመላ በሀገሪቱ በወባ መከላከል ላይ በተሠራው ተግባር የበርካታ ዜጎችን ሕይወት መታደግ ተችሏል ብለዋል።
ከወባ መከላከል በተጨማሪ በኤች አይ ቪ፣ በግል እና አካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ፣ በንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ድልድዮችን ጭምር በመሥራት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
በሥነ ተዋልዶ ጤና፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናትን በመደገፍ፣ በጸረ ትንባሆ ዘመቻ፣ የሕክምና ቁሳቁስ በማጓጓዝ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራ እየሠራ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
ማኅበሩ በአንድ ክልል የጀመረውን ሥራ አሁን ላይ በ10 ክልሎች በማስፋት ማኅበራዊ ግዴታውን እየተወጣ መኾኑንም ገልጸዋል።
በውስን በጎ ፈቃደኞች የተጀመረው ሥራም አሁን ላይ 260 ሺህ አባላትን በማስተባበር በጸጥታ እና ሌሎች ምክንያቶች እየተባባሰ የመጣውን የወባ ሥርጭት በራስ አቅም የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!