ለ25 ዓመቱ የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱ መሳካት በእልህ እና በቁጭት ልንሠራ ይገባል።

7

ወልድያ: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳደር የመንግሥት እና የፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዝግጅት ግምገማ እየተካሄደ ነው።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር በ2017 በጀት ዓመት ለመፈጸም ከታቀዱት የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሰላም ተግባራት ላይ አበረታች ውጤቶች የተገኘባቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ወደፊትም ችግሮችን በድል አድራጊነት እየተወጣን፣ አርቀን በማየት እና አልቀን በመሥራት የዞናችንን ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንሠራለን ነው ያሉት።

በግብርና፣ በፕሮጀክት አፈጻጸም፣ በኢንቨስትመንት፣ በፖለቲካ፣ በሕዝብ ግንኙነት እንዲሁም የዞኑን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ከሌሎች ዞኖች ጋር ተወዳድሮ ዞኑ ሦስተኛ መውጣቱንም በዕለቱ ገልጸዋል።

የዚህ የግምገማ መድረክም በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ ተግባራት የነበሩ ክፍተቶችን ለማረም እና ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደኾነ ተናግረዋል። የ2018 የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ለመምከር የተዘጋጀ መኾኑንም ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅዶቻችንን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ከድር ሙስጦፋ ለ2017 በጀት ዓመት ስኬት ከቀበሌ እስከ ዞን ያሉት የሥራ ኀላፊዎች እና የኅብረተሰቡ የላብ እና የደም ዋጋ ውጤት እንደነበር አስረድተዋል።

በቀጣይም በሚያጋጥሙ ፈተናዎች ሳንበረከክ ዞኑ መልማት በሚገባው ልክ ለምቶ ማኅበረሰቡን በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የምንሠራበት ሊኾን ይገባል ብለዋል። ለክልሉን “የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ የልማት ዕቅድ መሳካት በእልህ እና በቁጭት ልንሠራ ይገባል” ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው ሰሜን ወሎ ዞን በ2017 በጀት ዓመት ፈታኝ ጊዜን እያሳለፈ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን በመሥራት ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ለቀጣይ ተግባራት መሠረት ነው ብለዋል።

2018 በጀት ዓመትም እንደ ሀገር ከተስፋ ብርሃን ወደ ሚጨበጥ ብርሃን የመጣንበት ዘመን ነው ያሉት አቶ እርዚቅ እየገጠመን ያለውን የድህነት እና የሰላም ችግር ለመቅረፍ የምንሠራበት ዘመን ነውም ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ መሪዎች የክልሉን የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ሰላምን ማስፈን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መኾኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በልማት፣ በመልካም አሥተዳደር እና ብቁ መሪ ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን ነው ያሉት።

በ2018 በጀት ዓመት ሰላምን ማጽናት፣ ብልሹ አሠራርን መታገል፣ መልካም አሥተዳደርን ማስፈን እንዲኹም የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀም ለውጤት አብቅቶኛል” ከፍተኛ ውጤት ያስመገበች ተማሪ
Next articleየማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።