“ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀም ለውጤት አብቅቶኛል” ከፍተኛ ውጤት ያስመገበች ተማሪ

28

ደሴ፡ መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር አቀፍ ፈተናን በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት መስክ 577 ውጤት ማስመዝገብ ችላለች ተማሪ አና ብሩክ።

በ2017 የትምህርት ዘመን በደሴ ከተማ የመምህር አካለ ወልድ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዋ አና ብሩክ ለተገኘው ውጤት ዋነኛው ምስጢር ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እና በቂ ዝግጅት ማድረግ መኾኑን ነው ከአሚኮ ጋር በነበራት ቆይታ የገለጸችው።

“ጊዜዬን በአግባቡ እጠቀም ነበር፤ ውጤታማ የኾንኩትም በዚህ ምክንያት ነው፤ ወደፊትም ብቁ ዜጋ ሆኜ ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ” ብላለች።

ተማሪ አና ለስኬቷ ወላጆቿ ወይዘሮ ብርቱካን ይኸይስ እና አቶ ብሩክ አደራ ያደረጉላት ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጻለች።

ወላጆቿ አጋዥ መጻሕፍትን ከመግዛት ጀምሮ ለጥናት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ ትልቅ ሚና እንደተጫወቱም ነው ያስገነዘበችው።

መምህራን አሁን ለተገኘው ውጤት ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ገልጻለች።

የተማሪ አና ወላጆችም ልጃቸው በትምህርት ላይ እንድታውል አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ከትምህርቷ ሊያዘናጋ የሚችል ማንኛውንም ነገር እንዳትጠቀም ይመክሯት እንደነበርም ጠቁመዋል።

በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሟ ከትምህርት ጋር የተያያዘ ብቻ መኾኑ ለስኬቷ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት።

የአና ስኬት በቤተሰብ ውስጥ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን የገለጹት ወላጆቿ ታናሽ ወንድሟ አዶኒያስ ብሩክም የእህቱን አርዓያ በመከተል በ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና 98 ነጥብ 33 አማካይ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

አዶኒያስም የእህቱ ጎበዝ ተማሪ መኾን እርሱም እንዲጠነክር እንዳደረገው ገልጿል።

ዘጋቢ: ደጀን አምባቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ማምጣቱ ላይ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል።
Next articleለ25 ዓመቱ የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱ መሳካት በእልህ እና በቁጭት ልንሠራ ይገባል።