ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ማምጣቱ ላይ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል።

9

ባሕር ዳር: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በአማራ ክልል ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎችን ለመመለስ ቅንጅታዊ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የትምህርት ባለድርሻዎች ይገልጻሉ።

በምዕራብ ጎንደር አሥተዳደር ዞን ቋራ ወረዳ የገለጉ ከተማ ዙሪያ ነዋሪው አምላኩ ወርቁ በጸጥታ ችግር የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ መቆየቱን ለአሚኮ አስታውሷል።

ተማሪው ትምህርት በማቋረጡ ቢቆጭም አሁን ግን ትምህርት ቤት ተከፍቶ ያቋረጠውን ትምህርት በመጀመሩ ደስታ ተሰምቶታል።

“ሁለት ዓመት ሙሉ ትምህርት አቋርጨ ባልከርም ኑሮ ዘንድሮ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል ነበረኝ” የሚለው ተማሪ አምላኩ በቀሪው ዘመን ብሩሕ ተስፋን ሰንቋል።

በምሥራቅ ጎጃም አሥተዳደር ዞን ጎዛምን ወረዳ የፋና አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሐይማኖት እጅጉ በበኩላቸው ትምህርት ከመቋረጡ በፊት የአምስተኛ ከፍል የተማሪዎች ስም ተቆጣጣሪ እና ሒሳብ ያስተምሩ እንደነበር ተናግረዋል።

ከአንድ ዓመት ትምህርት መቋረጥ በኋላ በ2018 ዓ.ም ትምህርት ሲጀመር ያኔ ከነበሩት ተማሪዎች መካከል ትምህርት የጀመሩት 20 ተማሪዎች ናቸው በማለት አሁንም ተማሪዎችን የመመለሱ ሥራ በርብርብ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ሌላዋ አስተያዬት ሰጭ በሰሜን ጎጃም አሥተዳደር ዞን ሰሜን አቸፈር የሚያስተምሩት መምህርት ያየሽ ስዩም በጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት ከመቋረጡ በፊት 7ኛ ክፍል ውስጥ 75 ተማሪዎችን ስም እየተቆጣጠሩ እንግሊዝኛ ቋንቋ ያስተምሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከአንድ ዓመት ትምህርት መቋረጥ በኋላ የ2018 ዓ.ም ትምህርት ዘመን ሲጀመር በዚያ ክፍል ውስጥ ለመማር ተመዝግበው ያገኟቸው ተማሪዎች 15 ብቻ ናቸው።
ይህ አሐዝ የተማሪ ምዝገባውን ሁሉም በርብርብ ማከናወን እንዳለበት አመላካች ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በምሥራቅ ጎጃም አሥተዳደር ዞን የመምህራን ማኀበር ሊቀ መንበር መብት የኸይስ ማኀበሩ በሚያገኘው አጋጣሚ ኹሉ ትምህርት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነጻ መኾኑን እያስረዳ ወላጆች ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ፣ መምህራንም መማር ማሰተማር ብቻን እንዲያስቀጥሉ በማድረግ ላይ ነው ብለዋል። በመኾኑም ተዘግተው የነበሩ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ሙያዊ ኀላፊነታቸውን እየተወጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በርብርብ በመሠራቱም በዞኑ አሁን ላይ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውን ነው አቶ መብት የተናገሩት።

የክልሉ መምህራን ማኀበር ምክትል ፕሬዝዳንት እናውጋው ደርሰህ ሁሉም ዜጋ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ማድረግ ከማኀበሩ ዓላማዎች መካከል መኾናቸውን አንስተዋል። ትምህርት ደግሞ የሰው ልጆች ሁሉ የተጎናጸፉት ሰብዓዊ መብት በመኾኑ በሰዎች ይሁንታ የሚሰጥ እና የሚነፈግ አይደለም ነው ያሉት።

ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሁሉም አካል ትምህርት እንዳይቋረጥ መሥራት ይኖርበታል።

“ሀገር በዕድገት ጎዳና መገስገስ የምትችለው፣ ዜጎችም የተሻለ ሕይዎት የሚኖራቸው፣ ከዓለም ሀገራት ጋር እኩል መራመድ የሚቻለው፣ የታፈረች፣ የተከበረች እንዲኹም ሰላማዊ ኢትዮጵያን መገንባት የሚቻለው የተማረ ኀብረተሰብ ሲኖር ብቻ ነውም”ብለዋል። ስለዚህ ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ትምህርትን መደገፍ እና ማበረታታት ይገባዋል ነው ያሉት።

ማኀበሩ እስከ ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር በተገኘው አጋጣሚ ኹሉ የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማትን እና የትምህርት ሴክተሮችን በመያዝ የተቋረጠው ትምህርት እንዲቀጥል ስለመንቀሳቀሱም አስገንዝበዋል።

በዚህም በርካታ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ተደርጓል። ከትምህርት ገበታ ወጭ የነበሩ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ትምህርት እንዲጀምሩ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል ብለዋል። ወደፊትም አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾን ሥራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ያስገነዘቡት።

ሁሉም አካላት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና ትምህርት እንዲጀምሩ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፈንቴ አምባው ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት ትምህርት በመቋረጡ ከ60 በመቶ በላይ ተማሪዎች ለሥነ ልቦና ጫና እና ጭንቀት ተዳርገዋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች ትምህርት ከተቋረጠ ከሁለት ዓመት በላይ በመኾኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ካሁን ቀደም ያካበቱት ዕውቀት ምን ያህል እንደባከነባቸው መገመት አይከብድም ብለዋል።

“እስከ አሁን የትምህርት ስብራቱ ከፍተኛ የትምህርት ብክነት እና ኪሳራ አድርሷል” ያሉት ፕሮፌሰር ፈንቴ ከእንግዲህ ትምህርት ላቋረጡ ተማሪዎች ያለው ተስፋ በ2018 መማር ይኾናል። ስለዚህ ሁሉም በርብርብ ልጆችን ማስተማር አለበት፤ አለበለዚያ የሚደርሰውን የትውልድ ክፍተት መቼውንም መሙላት አይቻልም ነው ያሉት።

ማንም ይኹን ማን ትምህርትን በማቋረጥ ኪሳራ እንጅ የሚያገኘው ጥቅም ባለመኖሩ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ እንደኾነም አብራርተዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኀበራዊ ዘርፍ እስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በ2016 የትምህርት ዘመን 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር ቢታቀድም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚኾኑት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመምጣቸውን አስታውሰዋል።

በ2017 ዓ.ም ደግሞ ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር መታቀዱን ያስታወሱት ዶክተር ሙሉነሽ 4 ሚሊዮን የሚኾኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መምጣት አልቻሉም። ከተመዘገቡት ተማሪዎች መካክልም ብዙዎቹ ማቋረጣቸውን ተናግረዋል።

በ2018 የትምህርት ዘመን ታዲያ ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ገበታ ርቀው የነበሩ ተማሪዎችን በማካተት 7 ሚሊዮን 445 ሺህ 545 ተማሪዎችን ለማስተማር መታቀዱን ነው ቢሮ ኀላፊዋ ያመለከቱት፡፡

ከነሐሴ አጋማሽ 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ ርብርብም 3 ሚሊዮን ያክል ተማሪዎች መመዝገባቸውን ነው ዶክተር ሙሉነሽ የተናገሩት። አሁንም ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ሁሉም መረባረብ እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በጎንደር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ።
Next article“ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀም ለውጤት አብቅቶኛል” ከፍተኛ ውጤት ያስመገበች ተማሪ