
ደሴ: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኛው የ2017 ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 ዕቅድ ትውውቅ መድረክ ከሕዳሴው ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ማግስት የይቻላል መንፈስን አዳብረን የምናካሂደው ስለኾነ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
ክልሉን የሚገጥሙትን የሰላም እና ጸጥታ ችግር ለመቅረፍ እና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አሻጋሪ ዕቅድ የታቀደበት ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ ተስፋ ዕቅዱን በተግባር ለመፈጸም በውይይቱ ንቁ ተሳታፊ መኾን እንደሚገባ ነው ያስረዱት።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን በ2017 ዓ.ም በክልል ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ሥራዎች የተሠሩበት መኾኑን ገልጸው ዞኑ በክልል ደረጃ ከፍተኛ አፈጻጸም አስመዝግቦ በክልሉ መንግሥት እውቅና እንደተሰጠው አስታውሰዋል።
አማራ ክልል የገጠመውን ብርቱ ፈተና ለማለፍ የዞኑ የሥራ ኀላፊዎች መላ ሕዝቡን በማሥተባበር ከገባንበት ፈተና ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ለተመዘገበው ስኬት የመሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኛው እና ሕዝቡ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል ነው ያሉት።
በሕዝብ እና በፓርቲ መካከል መተማመን እንድፈጠር ውጤታማ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መከናወኑንም አንስተዋል። የግብርና ልማትን በማሳደግ እና ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል።
የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ ጤናማ ማኅበረሰብ ለማፍራት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ ብሎም ተረጅነትን ለማስቀረት ፍሬያማ ሥራ መሠራቱን አቶ አሊ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በርካታ ድሎች እና ስኬቶች ተመዝግበዋል ያሉት አቶ አሊ ይህንን ስኬት በ2018 በጀት ዓመት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ነው ያስታወሱት።
የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለመጨመር እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መሠራት እንዳለበትም ገልጸዋል። “ሥራ አጥነትን እና ኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ቆርጠን መሥራት አለብን” ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅም አስታውሰዋል።
የዞኑን ብሎም የክልሉን ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም በማሸጋገር ሕዝቡን ከችግር ማላቀቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የ25 ዓመቱ አሻጋሪ እና የእድገት ዕቅድ ክልሉ የሚደርስበትን እድገት ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት አቶ አሊ በ2042 ልንደርስበት ያሰብነውን ሁለንተናዊ ለውጥ እውን ለማድረግ የመጀመሪያውን አምስት ዓመት አፈጻጸም በዚህ በጀት ዓመት በተግባር ጀምረነዋል ነው ያሉት። ለዚህ ስኬት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ በኢትዮጵያዊያን የጋራ ትብብር ታላቁ የሕዳሴ ግድብን አጠናቀን የአሸናፊነት መንፈስን በሰነቅንበት ወቅት የሚካሄድ መድረክ ስለኾነ ውይይቱን የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን በ2017 በጀት ዓመት ላስመዘገበው ስኬትም እንኳን ደስ አላችሁ ነው ያሉት።
በፓርቲ እና በመንግሥት ሥራዎች የተመዘገበው ውጤት ከላይ እስከ ታች ያለው መዋቅር ቅንጅታዊ ስኬት መኾኑን ያነሱት ምክትል አፈ ጉባኤው በስኬቱ ሕዝቡ ተጠቃሚ መኾኑንም ገልጸዋል።
የዞኑን ሰላም የተሟላ በማድረግ በኩል በትኩረት መሠራት እንዳለበትም አንስተዋል። የጽንፈኞችን አስተሳሰብ በማምከን እና የቡድኑን ድብቅ አጀንዳ በማጋለጥ በኩል የዞኑ መሪዎች ከፍተኛ ሥራ አከናውነዋል ያሉት አቶ አማረ ተግባሩ ለሰላም እሴት ግንባታ ትልቅ ሚና ማበርከቱንም ገልጸዋል።
የዞኑን ውጤታማ አፈጻጸም በክልል ደረጃ መተግበር እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!