
ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር” አርቆ ማየት፣ አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልዕክት የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር መሪዎች በችግር ውስጥ ኾነው፣ በአንድ ላይ ቆመው በ2017 ዓ.ም ጥሩ አፈጻጸም እንደነበራቸው ገልጸዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ነዋሪዎች በሁሉም ተግባራት አጋዥ እንደነበሩ ጠቅሰዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ላደረጉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። 2017 ዓ.ም እንደ ሀገር እና እንደ ከተማ የውጤት ዓመት መኾኑንም ገልጸዋል። በ2018 ዓ.ም ይህን ጥንካሬ ማስቀጠል እንደሚገባ እና የበለጠ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት። በዓመቱ “ሠርተን የምናሳይ መሪዎች መኾን ይገባናልም” ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከክልሉ መንግሥት የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ እና የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ የተቀዳ ለባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ምላሽ የሚሰጥ ዕቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማጠናቀቅ፣ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት፣ ሥራ አጥነትን ማቃልል እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት በልዩ ሁኔታ የሚሠራበት ዓመት እንደሚኾንም ተናግረዋል።
የጸጥታ፣ የሰላም ጉዳይ እና ትውልድ ግንባታ ላይም በትኩረት እንደሚሠራ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!