በዩኒቨርሲቲዎች ከ10 ሺህ በላይ የቃል ኪዳን ቤተሰብ መፈጠሩን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

5

አዲስ አበባ: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ማብሰሪያ መርሐ ግብር በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የማብሰሪያ ሥነ ሥርዓቱን ይፋ ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ድኤታው ከይረዲን ተዘራ (ዶ.ር) ናቸው። ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ያደረገችው እና ሕዳሴ ግድብን በስኬት ያጠናቀቀችው በኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ ለዘመናት ጠብቃ ያቆየቻቸው ባሕሎች፣ እምነቶች እና እሴቶች ባለቤት እንደኾነችም ተናግረዋል።

እነዚህ እሴቶች በማኅበራዊ ሚዲያ በሚተላለፉ የተዛቡ አስተሳሰቦች እና ትርክቶች የመሸርሸር አደጋ ተጋርጦባቸዋል ነው ያሉት ሚንስትር ድኤታው።

ይህንን አደጋ ለመከላከል እና ለመቀነስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በስድስት ዙሮች ተግባራዊ ባደረገው የቃል ኪዳን ቤተሰብ ከ3 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ማኅበራዊ ቤተሰብ መፍጠር እንደቻለም አንስተዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ይህን ተሞክሮ ለማስፋት ባደረገው ጥናት ፕሮጀክቱ በተጨባጭ ማኅበራዊ ትስስር መፍጠሩን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል።

ይህን መነሻ በማድረግም በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በጎንደር ከተማ ተገኝተው ተሞክሮ እንዲወስዱ ተደርጓል ነው ያሉት።

ተሞክሮውን መነሻ በማድረግም “በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከ10 ሺህ በላይ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ተፈጥሯል” ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከመደበኛው የመማር ማስተማር ኀላፊነታቸው ባሻገር ሀገር እንድትጸና እና ሰላም እንዲረጋገጥ ለማኅበረሰባዊ ትስስር እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መረጋገጥ በልዩ ትኩረት እንዲሠሩ መርሐ ግብሩ ይፋ መደረጉንም ገልጸዋል።

በተለይ በራስ ገዝነት የዩኒቨርሲቲ የውድድር ዘመን ተመራጭ እና ተወዳዳሪ ለመኾን ከመማር ማስተማር ሥራዎች ባሻገር ለማኅበራዊ ትስስር እና ለሰላም መስፈን በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ከተማ አሥተዳደሮችም በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት ተመራጭ ለመኾን ወደ እናንተ መርጠዋችሁ የሚመጡ ተማሪዎችን ከመቀበል ባሻገር ቤተሰባዊ ትስስር እና ትውውቅ በመፍጠር ለሀገራዊ አንድነት ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።

በዕለቱ የተገኙት የአዳማ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ማቲያስ ሰቦቃ ከተማዋ የመቻቻል፣ የአብሮነት እና የብዝኀነት መገለጫ ናት ብለዋል።

በከተማዋ ከሚገኘው የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ተማሪዎችን በፍቅር የመቀበል ልምድ ባለቤት ነን ነው ያሉት።

በቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክት ሀገራዊ ማብሰሪያ መርሐ ግብሩ የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና የከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ኢብራሒም ሙሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕገ ወጥ የንግድ መረቦችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ማስገባት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል።
Next articleትጋት፣ ቁርጠኝነት እና ቁጭት ያነገበ መሪ ማፍራት ያስፈልጋል።