ሕገ ወጥ የንግድ መረቦችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ማስገባት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል።

3

ደሴ: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ፍትሐዊ፣ ጤናማ እና ተደራሽ የንግድ ግብይት ሥርዓትን በማስፈን ገበያን ማረጋጋት” በሚል መሪ መልዕክት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ አካሂዷል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮናስ እንዳለ መምሪያው በ2017 በጀት ዓመት በርካታ ስኬታማ ተግባራት እንዳከናወነ ተናግረዋል። የኑሮ ውድነትን በማቃለል እና ሕገ ወጥነትን በመከላከል ረገድ የሚስተዋሉ ድክመቶች ትኩረት የሚሹ የተቋሙ የቀጣይ የቤት ሥራዎች እንደሚኾኑም አንስተዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የተቋሙ ሥራ ከማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ኑሮ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመኾኑ በብዙ መልኩ ይፈተናል ብለዋል። ተቋሙን በሁለንተናዊ መልኩ በመደገፍ በተሻለ መልኩ እንዲሠራ ማገዝ ይገባል ነው ያሉት።

ከተማ አሥተዳደሩ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመኾን ለገበያ ማረጋጋት ሥራ ቁልፍ ሚና የሚጫወት የግብይት ማዕከል እያስገነባ እንደኾነም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ቀለመወርቅ ምህረቴ የደሴ ከተማ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የተሻለ መፈጸሙን አንስተዋል። በቀጣይም በትጋት በመሥራት ውጤታማ ተግባርን መፈጸም ይገባል ብለዋል።

በተለይ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት እና ሕገ ወጥ የንግድ መረቦችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ማስገባት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

በመድረኩ የላቀ ውጤት ለነበራቸው ክፍለ ከተሞች፣ የሥራ ቡድኖች፣ ባለሙያ እና መሪዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ:- ጀማል ይማም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመሳላ በዓል በዱራሜ ከተማ እየተከበረ ነው።
Next articleበዩኒቨርሲቲዎች ከ10 ሺህ በላይ የቃል ኪዳን ቤተሰብ መፈጠሩን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።