
አዲስ አበባ: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመሳላ በዓል በከምባታ ብሔር ዘንድ በልዩ ዝግጅት እና ክብር የሚታጀብ ታላቅ በዓል ነው።
በአካባቢው ባሕል መሠረት የዘር ወራት እንዳበቃ እረኞች ዋሽንት (ገምባቢያ) መንፋት ይጀምራሉ። በየስፍራውም በተለይ በስንደዶ (ዱፋ) ውስጥ “ዘራሮ” ተብለው የሚታወቁ ነጭ ቀለም ያላቸው የመስክ አበቦች ማበብ ይጀምራሉ። ይህም የመስቀል በዓል መቃረቡን የሚያመለክቱ ምልክቶች ናቸው።
አስቀድሞ በክረምት ወራት የእርድ ከብቶች በየቤቱ ታስረው መቀለብ እና ማድለብ መጀመርም ሌላው የመስቀል በዓል መቃረብ ምልክት ነው። ለመስቀል በዓል ወንዶች እና ሴቶች የየራሳቸውን ዝግጅትም ይቀጥላሉ።
በዓሉ የመስከረም 1 ቀን የዘመን መለወጫ በዓል (ሌንጃ) ከገባበት ጊዜ አንስቶ ልዩ ልዩ መሰናዶዎች ይደረጉበታል።
ለመስቀል በዓል ሲባል በጊዜ ታስቦ እና ታቅዶ የእርድ ከብቶችን መቀለብ እና በደንብ ማድለብ የታወቀ እንደመኾኑ መጠን ከሰኔ ወር ጀምሮ ከቤት የማይወጡ ከብቶችን በየቤቱ ማየት የተለመደም ይኾናል።
ከዚህም ሌላ ለመስቀል በዓል ተብሎ ጥሩ የግጦሽ መሬት ተከልሎ እና “ክልክል የሣር ስፍራ” ወይም “ከሎ” ተብሎ ተሰይሞ በመስቀል በዓል ወቅት ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ ከብቶችም የሚደሰቱበት ጊዜ እንዲኾንላቸው ጥሩ የሣር ግጦሽ ይዘጋጅላቸዋል።
በሌላ በኩል በየጫካው ዛፎችን በመቁረጥ እና በመፍለጥ በቂ የማገዶ እንጨት ይዘጋጃል። እያንዳንዱ ቤተሰብ ለበዓሉ አከባበር የሚበቃውን ያህል የማገዶ እንጨት ይሰበስባል፣ በየደጃፉም ይቆልላል።
ወጣቶች ለደመራው በዓል ዕለት ችቦ በብዛት ከየጫካው ይሰበስባሉ፤ መሰብሰብ ለማይችሉ እና ለዚህ ተግባር የሚሰለፉ ልጆች ለሌሏቸው ቤተሰቦች ደግሞ በነጻ ያድላሉ። በከተሞች እንደሚደረገው ችቦዎችን መሸጥ ነውር ነው፤ በዚህም ምክንያት አቅም ለሌላቸው ጎረቤቶች በነጻ ያቀርቡላቸዋል። ወጣቶች እጅግ ከሚደሰቱባቸው እና የበዓሉን ምንነት ከሚያንጸባርቁባቸው መንገዶች አንዱ የችቦ ለቀማ ፕሮግራም ነው።
በዓሉ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የነጻነት፣ የአንድነት እና የመከባበር በዓል ሲኾን ሴቶችም ኾነ ወንዶች በተለያዩ አልባሳት ደምቀው ልዩ ልዩ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ በተለያዩ ሁነቶች የሚከበር በዓል ነው።
የመሳላ በዓል በከምባታ ብሔር ዘንድ በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ በከፍተኛ ዝግጅት እና ድምቀት በከምባታ ዞን በዱራሜ ከተማ ዛሬ ላይ እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ፣ የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቡቶ አኒቶ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አንተነህ ፈቃዱ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና በክልሉ ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ.ር)፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ድኤታ ነፊሳ አልማህዲ፣ የክልል የዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የሌሎች ብሔሮች ተወካዮች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- ልድነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!