“ፈተናዎች ቢበዙም እንኳ ካስቀመጥነው ግብ ለመድረስ ብርቱ መኾንን ያሻል” ውጤታማው ተማሪ

14

ደሴ: መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ ኢብራሒም ሙሐመድ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ገርባ ከተማ በሚገኘው የአልነጃሽ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማረው።

በ2017 ዓ.ም በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 576 ነጥብ 39 በማስመዝገብ የላቀ ውጤት ማምጣት ችሏል።

በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከሚኖርበት አካባቢ ተፈናቅሎ ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ መምጣቱን የሚናገረው ተማሪ ኢብራሒም ያለፈበት መንገድ አስቸጋሪ እንደነበር ያስታውሳል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የላቀ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል መኾን የቻለው ተማሪ ኢብራሒም “በችግር ውስጥ ባልፍም የተሻለ ውጤት ማምጣት ችያለሁ” ብሏል ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ። ሌሎች ተማሪዎችም ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ለስኬት መብቃት እንደሚችሉ ይመክራል።

“በሕይወት መንገዳችን ላይ መሰናክሎች ቢበዙም እንኳ ካስቀመጥነው ግብ ለመድረስ ብርቱ መኾንን ያሻል” የሚል ጽኑ አቋም እንዳውም ተናግሯል።

በትምህርት ሕይወቱ ዙሪያ ተሞክሮውን ያጋራው ተማሪ ኢብራሒም ሙሐመድ የተሻለ ውጤት የማስመዝገቡ ቀዳሚ ምክንያት ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀሙ መኾኑን አንስቷል። በክፍል ውስጥም ያልተረዳውን በመጠየቅ እና በትኩረት በማንበብ ለሀገር አቀፍ ፈተና ሲዘጋጅ እንደነበርም አስታውሷል።

ተማሪ ኢብራሒም ከተፈተናቸው ስድስት የትምህርት ዓይነቶች መካከል ሒሳብ እና ፊዚክስን መቶ ማምጣት እንደቻለ ገልጾልናል።

ለሁለቱ የትምህርት አይነቶች የተለየ ፍቅር እንዳለው የሚያነሳው ኢብራሒም ተማሪዎች ለነዚህ ትምህርቶች ትኩረት መስጠት ከቻሉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ነው ምክረ ሃሳቡን ያጋራው።

ፈተናዎች ሳይበግሩት የላቀ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ኢብራሒም በቀጣይ የዩኒቨርሲቲ ቆይታው በርትቶ በማንበብ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ተግቶ እንደሚሠራም ገልጿል።

የተማሪ ኢብራሒም ወላጅ እናት ወይዘሮ ሰዓዳ ሁሴን ልጃቸው ባመጣው ውጤት መደሰታቸውን ተናግረዋል። “ልጄ ጎበዝ ተማሪ ብቻ ሳይኾን በመልካም ሥነ ምግባሩም ለታናናሽ እህት እና ወንድሞቹ አርዓያ ነውም” ብለዋል።

በአልነጃሽ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሒሳብ እና ፊዚክስ መምህርራን የኾኑት አምሳሉ ገድፉ እና መምህር ተመስገን መኮነን በተማሪ ኢብራሒም ውጤት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ከትምህርት ቤቱ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላል ብለው ይጠብቁት እንደነበርም አብራርተዋል። የመልካም ስብዕና ባለቤት እንደኾነ በመምህራኑ ምስክርነት የሚቀርብለት ተማሪ ኢብራሒም ሌሎች ጓደኞቹን ለማገዝ የሒሳብ ክበብ በማቋቋም ተማሪዎችን ያስተምር እንደነበር አስታውሰዋል።

ዘጋቢ፦ ሰልሀዲን ሰይድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቀለም ትምህርት ብቻ ጎበዝ መኾን በቂ አይደለም፡፡
Next articleየዓለም ቱሪዝም ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መከበር ጀመረ።