በቀለም ትምህርት ብቻ ጎበዝ መኾን በቂ አይደለም፡፡

4

ባሕር ዳር፡ መስከረም 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን አልፈው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉት ተማሪዎች 8 ነጥብ 4 በመቶዎቹ ብቻ መኾናቸውን ከሰሞኑ የትምህርት ሚንስትር አስታውቋል።

በመግለጫቸው ሙሉ በሙሉ ተማሪ ያላለፈባቸው እና ሁሉንም ተማሪዎች ያሳለፋ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ነበር። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ማበልጸጊያ ማዕከል (steem center) ደግሞ ያስፈተናቸውን ተማሪዎች በሙሉ ማሳለፍ ከቻሉ ትምህርት ቤቶች መካከል እንደኾነ የማዕከሉ ዳይሬክተር ዓለሙ ተስፋዬ (ዶ.ር) ነግረውናል።

በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ካስፈተናቸው 41 ተማሪዎች መካከልም ከ26 በላይ የሚኾኑት ከ500 በላይ የማለፊያ ነጥብ ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸውልናል።

በትምህርት ቤቱ በባሕር ዳር ዩኒቨርሳቲ ውስጥ የተሻለ የማስተማር ልምድ ያላቸው መምህራን ተመርጠው እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ከሚሰጡት የክፍለ ጊዜ ሰዓት በተለየ በማዕከሉ እንደሚጨምርም ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ መምህራን ትምህርቶችን ቀድመው እንዲጨርሱ፣ ቀደም ባሉ ዓመታት የተሰጡ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን ለመሥራት፣ ተከታታይ የሞዴል ፈተናዎችን በትምህርት ቤቱ ለመስጠት፣ ተማሪዎችን ለማዘጋጀት እና ውጤታማ ለማድረግ እንዳገዛቸውም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር ያጣነው ሀገር ተረካቢ ተማሪዎችን ማፍራት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ “በቀለም ትምህርት ብቻ ጎበዝ መኾን ለሀገር በቂ አይደለም ነው ያሉት፡፡ ሰብዓዊነት እና ሥነ ምግባር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ማበልጸጊያ ማዕከል ተማሪዎች በሥነ ምግባራቸው የተሻሉ እንዲኾኑ እና በሄዱበት ሁሉ ውጤታማ መኾን እንዲችሉ የምክር አገልግሎት እና አጫጭር የሥነ ምግባር ሥልጠናዎች እንደሚሰጡም ነግረውናል፡፡

ተማሪዎች ቀጣይ በሚገቡበት የትምህርት መስክ የፈጠራ ሥራ መሥራት፣ ተራማጅ የኾነ እውቀት ማምጣት፣ ለሀገር የሚጠቅም ነገር መሥራት እንዲችሉ ከዚህ ጀምሮ እየተመከሩ ልምምድ እንዲያድጉ ተደርጓልም ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ውጤታማ መኾኑን ተከትሎም ልጆቻቸው ወደ ማዕከሉ እንዲቀላቀሉ የሚጠይቁ ወላጆች መኖራቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ማዕከሉ የሚቀበላቸውን ተማሪዎች ቁጥር ከፍ የማድረግ ሃሳብ እንዳለው ነው የተናገሩት።

ተማሪ ናትናኤል አይዞህበል በዚሁ ትምህርት ቤት በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ተፈትኖ ከ600ው 556 በማስመዘገብ በትምህርት ቤቱ ተፈትነው ከነበሩ ተመሪዎች ባስመዘገበው ውጤት ሦስተኛ ኾኖ እንዳለፈ ነግሮናል፡፡

እንደ ሀገር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመቀላቀል የማለፊያ ነጥብ ካመጡ ተማሪዎች መካከል አንዱ በመኾኑ የተሰማውን ደስታም አጋርቶናል፡፡ በቀጣይ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ተቀላቅሎ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ለመማር ፍላጎት እንዳለው ገልጾልናል፡፡

አሁን ላይ ላስመዘገበው ጥሩ ውጤትም የቤተሰቦቹ እና የትምህርት ቤቱ እገዛ ከፍተኛ እንደኾነ ጠቅሷል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ማበልጸጊያ ማዕከል ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በተለየ ፈጠራ ሥራዎች እና ፕሮጀክቶች ላይ በማተኮር ተግባራዊ ትምህርቶችን መሥራት መቻል፤ ኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጅ ላይ ለየት ባለ መንገድ መማር መቻሉ ውጤታማ እንዳደረገውም ገልጿል፡፡

በክረምት ወቅትም የሮቦቲክ ሥልጠናዎች ሲያገኝ እንደነበር ተናግሯል። የመማር ማስተማሩን ሥራ የሚያግዙ እና የፈጠራ ሥራ ለመሥራት የሚያስችሉ በቂ የትምህርት ግብዓቶች በማዕከሉ መኖር ሀገር አቀፍ ፈተናውን በውጤታማነት ለማለፍ እና ጠቅላላ እውቀት ለመጨበጥ እንደረዳው ጠቅሷል።

ሌላኛዋ የ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና ተፈትና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ ሰላማዊት አያሌው ደግሞ ከ600ው 549 የማለፊያ ነጥብ አስመዝግባ ከትምህርት ቤቱ አራተኛ ደረጃን ይዛ እንዳለፈች ነግራናለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር እየቀነሰ መሄዱን ገልጻለች። በተያዘው ዓመትም ውጤት ሲገለጽ እና ያለፍትን ተማሪዎች ቁጥር ስትሰማ አስጨንቋት የነበረ ቢኾንም ያመጣችው ውጤት ደስታን እንደፈጠረላት ነግራናለች።

ሰላማዊት በቀጣይ የጤናውን የትምህርት ዘርፍ የመቀላቀል ፍላጎት እንዳላት ነው የተናገረችው። ከመጽሐፍ እና ደብተር ማሟላት ባሻገር ትምህርቷን ሊያግዙ የሚችሉ ግብዓቶች በቤተሰቦቿ እና በማዕከሉ መሟላታቸውም ውጤታማ ለመኾን ያገዟት ነገሮች እንደሆኑ ጠቅሳለች።

ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ላሉ ሌሎች ተማሪዎችም መምህራን ሲያስተምሩ በደንብ መከታተል፣ የማንበቢያ ዕቅድ፣ ሌሎችን ሰዎች የመጠየቅ ልምድ፣ የአጠናን ስልትን መምረጥ እና ከስህተት የሚማር ተማሪ መኾን ለውጤት እንደሚያበቃ መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስኬታማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲፈጠር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
Next article“ፈተናዎች ቢበዙም እንኳ ካስቀመጥነው ግብ ለመድረስ ብርቱ መኾንን ያሻል” ውጤታማው ተማሪ