ስኬታማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲፈጠር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

10
ጎንደር: መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት የአንድ ሀገር የስኬት መንገድ ነው። ብቁ እና ተወዳዳሪ ትውልድን ለመፍጠር ወሳኝ ሚናም አለው። ይሁን እንጂ የተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ አለመፈጠር እና የግጭት መበራከት ስኬታማ የመማር ማስተማር እንዳይኖር በማድረግ የተማረ የሰው ኀይልን ለመፍጠር እንቅፋት ይፈጥራል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ተማሪዎች ለሁለት ዓመታት በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ቆይተዋል። ይሄም በተማሪዎች ሕይወት ላይ ጫና ማሳደሩን የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተመልከት አዲስ ገልጸዋል።
በወረዳው ትምህርት ቤቶች በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን አንስተዋል። ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር የመጠገን እና ግብዓቶችን የማሟላት ተግባር መከናወኑንም አብራርተዋል። ወረዳው ከማኅበረሰቡ ጋር በትኩረት በመሥራት በ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ትምህርት እንዲጀመር መሠራቱን ጠቁመዋል። በዚህም በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 48 ሺህ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ33 ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በኅብረተሰብ ተሳትፎ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ለተማሪዎች ግብዓት መሟላቱን የገለጹት ደግሞ የጭልጋ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘሪሁን ንጉሤ ናቸው። ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት እንዲጀምሩ መሠራቱን አብራርተዋል። በወረዳው 56 ሺህ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስካሁን ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ2018 የትምህርት ዘመን ከ846 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ከ345 ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክንዱ ዘውዱ ተናግረዋል።
ከመስከረም 5 ጀምሮ በዞኑ ትምህርት መጀመሩንም ገልጸዋል። ተመዝግበው ወደ ትምህርት ገበታ ያልመጡ ተማሪዎች እንዲመጡ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል። ባለፈው የትምህርት ዘመን ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በ2018 የትምህርት ዘመን ወደ ሥራ ያልገቡ ትምህርት ቤቶችን ለማስጀመር ይሠራል ነው ያሉት።
“የትኛውም አካል ለትምህርት ባለቤት ነው” ያሉት ኀላፊው ለትምህርት ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል። ለተማሪዎች የትምህርት ግብዓትን በወቅቱ የማድረስ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል። የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል። በክረምት በጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት ማኅበረሰቡ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ.ር) ከመስከረም 9 ቀን ጀምሮ ለሁለት መሪዎች ሹመት ሰጡ።
Next articleበቀለም ትምህርት ብቻ ጎበዝ መኾን በቂ አይደለም፡፡