
ገንዳ ውኃ: መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ተግባራት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በገንዳ ውኃ ከተማ ተካሂዷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በርካታ የሕዝብ ግንኙነት ተግባራትን በመሥራት ሰላም እንዲሰፍን እና የአካባቢው ማኅበረሰብ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን መሠራቱን ተናግረዋል። በቀጣይ ማኅበረሰቡ ለሰላም መከበር ከመንግሥት ጎን በመቆም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል። በቀጣይ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ እንደኾኑም ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንዳለው ማሩ ሰላምን ለማስፈን ከፍተኛ የኾነ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ማካሄድ እንደተቻለ ተናግረዋል። በቀጣይም ዞኑ ያለውን “ጸጋ አሟጦ በመጠቀም ማኅበረሰቡን የልማት ተቋዳሽ ማድረግ” ያስፈልጋል ብለዋል።
ማኅበረሰቡ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን ከፍተኛ የኾነ የገቢ አሰባሰብ ሥራዎች ተጠናክረው መሠራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የክልሉን የ25 ዓመት ዕቅድ ለማሳካት የሚሠሩ ተግባራትን ጥራት ባለው እና ፍጥነት በተሞላበት አግባብ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ ግምገማው የነበሩ ክፍተቶችን ለማረም፣ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እና የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ትኩረት ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ማኅበረሰቡ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሰፊ ሥራ ሢሠራ ቆይቷል ነው ያሉት።በቀጣይም ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት እና ሰላም እንዲረጋገጥ በማድረግ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች፣ መንገዶች እንዲከፈቱ፣ ፍትሐዊነት እና ተጠያቂነትን መሠረት ያደረገ የመልካም አሥተዳደር ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!