“ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ለሕዝብ ተጨባጭ ለዉጥ ማምጣት ይገባል”

3
ደብረ ብርሃን፦ መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2018 እቅድ ትውውቅ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ሰሜን ሸዋ ዞን ባከናወነው ውጤታማ ሥራ በክልል ደረጃ በቅርቡ በተካሄደው የእዉቅና መርሐ ግብር ላይ እውቅና ማግኘቱ ይታወሳል። ዞኑ ይህንን ዉጤት እንዲያስመዘግብ መሪው የነበረዉ ድርሻ የላቀ እንደነበር የሰሜን ሸዋ አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ ተናግረዋል ።የ2018 በጀት ዓመት እቅድን ዕዉን ለማድረግ መሪው ከፊት መሰለፍ ይኖርበታል ነዉ ያሉት።
በ2017 በጀት ዓመት መሪዎች ያጋጠማቸዉን ችግር በመሻገር የመምራት ጥበብን የተጎናፀፉበት ነበር ያሉት ደግሞ የዞኑ ብልፅግና ፅሕፈት ቤት ኀላፊ ኤሊያስ አበበ ናቸዉ። በ2018 በጀት ዓመት የሰሜን ሸዋ ዞን በሁሉም ዘርፍ የላቀ ዉጤት እንዲያስመዘግብ መሪዎች ከፍተኛ ኀላፊነት እንደተጣለባቸዉም አንስተዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በአማራ ክልል የርዕሰ መሥተዳድሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) “እንደመሪ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም መሥራት እና ለሕዝብ የሚጠቅም ተጨባጭ ለዉጥ ማምጣት ይገባል” ብለዋል።
የትዉልድ ቅብብሎሹን የተከተለ አሻራን ለማሻገር ዉጤታማ የሚያደርግ የመሪነት ጥበብን መከተል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለዚህም መሪዎች ቁርጠኛ በመሆን የመፈጸም አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል። የ2018 በጀት ዓመትን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ብስራት እንደጀመርን ሁሉ እንደ ሀገርና እንደ ክልል የላቀ ዉጤት ለማከናወን የሚያስችል ሥራ መሥራት ይገባል ነዉ ያሉት።
ዘጋቢ፦ ብርቱካን ማሞ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበ2018 ዓ.ም በትምህርት ሥራ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።
Next articleጸጋን አሟጦ በመጠቀም ማኅበረሰቡን የልማት ተቋዳሽ ማድረግ ያስፈልጋል።