በ2018 ዓ.ም በትምህርት ሥራ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።

6
ጎንደር: መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የ2017 ዓ.ም የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል።
ውይይቱ “አርቆ ማየት፣ አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
የጭልጋ ወረዳ አሥተዳዳሪ አዛናው አደባ ባለፈው ዓመት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደረጉ የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ እና የመስኖ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደረጎ መከናወኑን አመላክተዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ቀኑ ቢያድጎ ባለፈው በጀት ዓመት በተሠራው ተግባር በዞኑ ሴቶችን በማደራጀት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲኾኑ በማድረግ አበረታች ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ የውይይቱ ዓላማ በ2017 በጀት ዓመት የተሠሩ ተግባራትን በመገምገም መልካም አፈጻጸሞችን ማስቀጠል እና የታዩ ክፍተቶችን ደግሞ መሙላት የሚቻልበትን መንገድ ለመፍጠር ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ በእንስሳት እርባታ፣ በሰብል ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እና በ12ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤትን በማስመዝገብ የተሻለ አፈጻጸም እንደነበርም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የሰቆጣ ቃል ኪዳን አማካሪ ባዘዘው ጫኔ ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን እና የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
“የትምህርት ሥርዓቱ ከባድ ፈተናዎች እንደገጠሙት የተናገሩት አቶ ባዘዘው በ2018 ዓ.ም ውጤት ማስመዝገብ በሚያስችል መልኩ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ማህደር አድማሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኢትዮጵያ ያከናወነችው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ እንደ አሕጉራዊ ሞዴል ዕውቅና እንዲሰጠው መወሰኑ ተገለጸ።
Next article“ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ለሕዝብ ተጨባጭ ለዉጥ ማምጣት ይገባል”