
አዲስ አበባ፡ መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከጷጉሜን 03/2017 ዓ.ም እስከ ጳጉሜን 05/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል። ጉባኤውን የኢትዮጵያ መንግሥት እና የአፍሪካ ኅብረት በጋራ ያዘጋጁት ሲኾን ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚያን ተሳትፈውበታል።
በጉባኤው የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተም የኢትዮጵያ ፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ.ር) መግለጫ ሰጥተዋል። በጉባኤው ዓለም ለአፍሪካ መር የአየር ንብረት መፍትሄዎች ትኩረት እንዲሰጥ የሚጠይቅ የአዲስ አበባ ድንጋጌ (ዲክላሬሽን) ፀድቋል ብለዋል በመግለጫቸው።
ሚኒስትሯ እንዳሉት በድንጋጌው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአፍሪካን የአየር ንብረት አቅጣጫዎችን ለመተግበር እንዲሁም የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በገንዘብ ለመደገፍ ተግባራዊ ርምጃ እንዲወስዱም ተጠይቋል። የአፍሪካ መሪዎች አፍሪካ በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔዎችን እና በአፍሪካ የሚመሩ መፍትሔዎችን ለመውሰድ እና ገንዘብ ለማሠባሠብ ቃል መግባታቸውንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በጉባኤው አፍሪካ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ ሳትኾን የመፍትሄ ምንጭ እና መሪ መኾኗን ጠንካራ መልዕክት እንዳስተላለፈችም በመግለጫው ተመላክቷል። የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋም በተፈጥሮ ላይ የተመሠረቱ መፍትሔዎች ወሳኝ መኾናቸው ተገልጿል ነው ያሉት። ሚኒስትሯ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እንደ አሕጉራዊ ሞዴል ዕውቅና እንዲሰጠውም ተወስኗል ብለዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ፍትሕን ማረጋገጥ ብሎም የአፍሪካ መፍትሔዎችን መተግበር እና ቀጣይነት ያለው ብቁ መሪ ችግሩን ለመቋቋም ወሳኝ መኾናቸውም በጉባኤው አጽንኦት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኅብረት ቀጣይ የትኩረት መስኮችን ይፋ ማድረጋቸውን እና በዚህም ለሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች 50 ቢሊዮን ዶላር ሃብት በየዓመቱ የማሠባሠብ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል። ሚኒስትሯ እንደገለጹት መሪዎች በጉባኤው አፍሪካ እ.አ.አ በ2030 በዓለም የታዳሽ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት ያላትን ድርሻ ከ2 በመቶ ወደ 20 በመቶ ከፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤን ተከትሎም ኢትዮጵያ 32ኛውን እና እኤአ በ2027 የሚካሄደውን “የኮፕ 30” ጉባኤን ለማዘጋጀት መጠየቋም በመግለጫው ተጠቅሷል።
ዘጋቢ፦ ረሕመት አደም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!