ተማሪዎች በቁሳቁስ ችግር ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ሁሉም በርብርብ መሥራት አለበት።

3
ባሕር ዳር፡ መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እፎይታ የበጎ አድራጎት ማኅበር የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ለሚገኘው የቁልቋል ሜዳ አንደኛ ደረጃና መካከለኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፋ ገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ እና ከአቢሲኒያ ባንክ ሠራተኞች የተገኘ ሲኾን 227 ተማሪዎች ተደራሽ ኾኗል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) የእፎይታ የበጎ አድራጎት ማኅበር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለተማሪዎች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል። ትምህርት የነገ ትውልድ መገንቢያ ነው፤ በትምህርት ቁሳቁስ ምክንያት ልጆች ከትምህርት እንዳይቀሩ ከረጅ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሠራ ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ የሚኾኑ በርካታ ተማሪዎች ናቸው ያሉት ኀላፊው ይህንን ችግር ለመፍታት ሁሉም መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ዛሬ የተደረገውን ድጋፍ ላስተባበረው እፎይታ የበጎ አድራጎት ማኅበር እና ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ድጋፍ ያደረገው ገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ተወካይ ጓዱ ሽበሽ ተቋሙ ከተሰጠው መደበኛ ተግባር ጎን ለጎን የማኅበረሰባዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት ድጋፉን ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ድጋፉ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ያግዛል ነው ያሉት፡፡
የቁልቋል ሜዳ አንደኛ ደረጃና መካከለኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት አገሬ ነቃጥበብ በትምህርት ቤቱ ከ90 በመቶ በላይ የሚኾኑት ተማሪዎች ድጋፍ የሚሹ ናቸው። ትምህርት ቤቱ በራሱ አቅም ማገዝ ስለማይችል የተለያዩ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ድጋፍ እያደረጉላቸው መኾኑን አንስተዋል፡፡ በድጋፉም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲማሩ አድርጓል። በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ምክንያት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥርም በእጅጉ መቀነሱን ገልጸዋል፡፡ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የእፎይታ በጎ አድራጎት ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ ዘላለም ዋለ ማኅበሩ በጋዜጠኞች እና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች የተቋቋመ ሲኾን ዓላማውም ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለማገዝ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበሩ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብ ቁሳቁስና የንጽህና መጠበቂያ፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ በዛሬው ዕለትም በቁልቋል ሜዳ ትምህርት ቤት ሌሎች ረጂ አካላትን በማስተባበር ለ227 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን ደብተር እና 10 እስክብሪቶ ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ ይህንን ድጋፍ ወደፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሕዝብ እና መንግሥት በትብብር ሲሠሩ ማንሠራራት እና ብልጽግና አይቀሬ ነው።
Next articleኢትዮጵያ ያከናወነችው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ እንደ አሕጉራዊ ሞዴል ዕውቅና እንዲሰጠው መወሰኑ ተገለጸ።