ሕዝብ እና መንግሥት በትብብር ሲሠሩ ማንሠራራት እና ብልጽግና አይቀሬ ነው።

2
ደብረማርቆስ፡ መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 ዓ.ም የአሻጋሪ ዕድገት የዘላቂ ልማት የዕቅድ ውይይት መድረክ “አርቆ ማየት አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በሰላም ጊዜ ብቻ ሳይኾን ችግር ባጋጠመ ጊዜም በፈተናዎች ውስጥ ፀንተው በመቆም ለዞኑ ሁለንተናዊ ለውጥ በመትጋት ላይ ለሚገኙ መሪዎች ምሥጋና አቅርበዋል። የሀገር ምልክት የኾነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ በተመረቀ ማግስት ይህ የውይይት መድረክ መደረጉ ታሪካዊ ያደርገዋልም ብለዋል።
ሕዝብ እና መንግሥት ተባብረው ሲሠሩ የማንሠራራት እና የብልጽግና ጉዞ አይቀሬ ነው፤ ይህም ዕውን እየኾነ መምጣቱን መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው። ያለን ሃብት እና ፀጋ በወጉ ለይቶ ሕዝብን በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ጉዳዮችን በጥልቀት በመገምገም እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር ለውጥ እና ዕመርታ ማምጣት የሚያስችል የቀጣይ 25 ዓመታት አሻጋሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱንም አንስተዋል። በቀጣይም ዕቅዶችን እና የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀሞችን በአግባቡ በማየት እና በመፈተሽ ከራስ አቅም ጋር አጣጥሞ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ መፈፀም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቴክኖሎጂ እና ዲጂታላይዜሽን አቅምን በማስፋት ከነበረው የተለመደ እና ኋላቀር አሠራር መላቀቅ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በአንድ በኩል ሰላምን የማረጋገጥ እና በሌላ በኩል ደግሞ ልማትን የማፋጠን ተግባራትን አቀናጅቶ በትኩረት መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።
በ2017 በጀት ዓመት የታዩ ድክመቶችን በመፈተሽ እና የታዩ ጠንካራ አፈፃፀሞችን በማስፋት በ2018 በጀት ዓመት ውጤታማ አፈፃፀም ለማስመዝገብ መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል። በብልጽግና ፓርቲ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ በላይ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች እና የፓርቲው አባላት በጽናት አልፈው ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን አሳይተዋል ብለዋል። ዞኑ ካጋጠመው የሰላም ዕጦት እንዲወጣ መሪዎች ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተው ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንም አመላክተዋል። ፓርቲው ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ከሕዝብ ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች እና አባላት ሰፊ ርብርብ ስለማድረጋቸውም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአምራች ኢንደስትሪው ለከተማዋ ዕድገት አቅም እንዲፈጥር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
Next articleተማሪዎች በቁሳቁስ ችግር ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ሁሉም በርብርብ መሥራት አለበት።