
ደብረ ብርሃን፡ መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ እያደረገ ነው፡፡
በመድረኩ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በብዙ መመዘኛዎች ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡ በኢንቨስትመንት ፍሰት፣ በዋጋ ማረጋጋት እና በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ በኩል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተማ አሥተዳዳሩ ተራማጅ ሥራዎችን መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ የዘላቂ እና አሻጋሪ ዕቅዶችን መነሻ በማድረግ እና የከተማዋን ጸጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአዲሱ በጀት ዓመት ዕቅድ መዘጋጀቱን አቶ በድሉ ጠቁመዋል፡፡
ደብረ ብርሃን ከተማ በአምራች ኢንደስትሪው ፍሰት ትታወቃለች ያሉት አቶ በድሉ በዚህ በጀት ዓመት ዘርፉ ለከተማዋ ዕድገት ትርጉም ያለው ሚና እንዲኖረው በቅርበት ይደገፋል ብለዋል፡፡ ወደ ከተማዋ የሚመጡ እና ቀድመውም ማምረት የጀመሩ ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢው እና ከማኅበረሰቡ ጋር ጤናማ ግንኙነት ፈጥረው ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
ደብረ ብርሃን ከተማ የነዋሪዎቿን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ያስፈልጋታልም ብለዋል፡፡ በተለይም የመንገድ መሠረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት በበጀት ዓመቱ ትኩረት የሚደረግ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ የከተማዋን ሰላም እና ጸጥታን ማረጋገጥ ሌላኛው የበጀት ዓመቱ ዋና የዕቅዱ ትኩረት ስለመኾኑም አንስተዋል። ተጠያቂነት ያለው አሠራር በመዘርጋት፣ ብልሹ አሠራሮችን በመታገል ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እና የተቋማትን አቅም መፈጸም ማሳደግ ላይ ትኩረት ይደረጋልም ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፦ ወንዲፍራ ዘውዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!