
ባሕር ዳር: መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ እና የደስታ መግለጫ ሰልፍ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ የተለያዩ መልዕክቶች ተላልፈዋል። ግድቡ የሀገራዊ አንድነት ውጤት ነው፤ በኅብረት ችለናል፤ ለአንድ ዓላማ መቆም ከተቻለ የማይቻል ነገር እንደሌለ የታየበት ነው የሚሉ እና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል። የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጦፌ ሙሐመድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉንም ያስተሳሰረ እና አንድነትን ያጠናከረ ፕሮጀክት መኾኑን ገልጸዋል።
የሕዳሴ ግድቡ በርካታ ፈተናዎችን ያለፈ መኾኑንም አንስተዋል። ፈተናዎቹ እና ጫናዎቹ በቆራጥ አመራርና በኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ከዳር መድረሱን ገልጸዋል። ግድቡ የትውልድ አሻራ ያረፈበት የኅብረታችን ማሳያ ነው ብለዋል። ዘመን ተሻጋሪ የልማት ስኬት መኾኑንም ገልጸዋል። የግድቡ መጠናቀቅ በቀጣይ መንግሥት የወጠናቸውን ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ከሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የሶማሌ ክልል ፕሮጀክቶቹ ከሚከናወኑባቸው አካባቢዎች አንዱ በመኾኑ ሕዝቡ ትኩረቱን ልማት ላይ ማድረግ አለበት ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!